Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለመንግስት ጥያቄ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፥ ክረምት እየገባ በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደር ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለምንም ችግር እንዲደርስ ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የፌዴራል መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ተጠይቋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት በይፋ ጥያቄውን ያቀረበው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከክልሉ ህዝብ ተወካዮች፣ ከቢሮና ዞኖች አመራር አባላት፣ በተለያየ ቦታ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፣ ከትግራይ ምሁራን፣ ከባለሀብቶችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ምክክር ካደረገ በኋላ ነው ብለዋል።

አሸባሪው የህውሃት ቡድን በክልሉም ሆነ በሃገሪቷ ላይ የፈጠረው ውስብስብ ችግር ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሆኑን ያወሱት ዶክተር አብርሃም፥ ለዚህም እስከ አሁን በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ መፍትሄዎች ሲወሰዱ መቆየቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ህግ የማስከበር እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር በህግ የሚታዩ ጉዳዮችን በህግ መፍትሄ ለመስጠት ከጥፋት ሃይሉ ወንጀለኛ የሆነውን ለይቶ ወደ ህግ የማቅረብ ስራ ሲከናወን መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ በፌዴራል መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስታውሰው፣ በቀጣይም ፖለቲካ አማራጮችን ታሳቢ ማደረግና መፍትሄ እርምጃዎች የመውሰድ አስፈላጊነት ላይ እምነት መኖሩን ጠቁመዋል።

አያይዘውም “አሁን በተጨማሪ ሁኔታውና ጊዜውን የሚመጥን ተጨማሪ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ጠቁመው፥ ክረምት እየመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዚህ ክረምት ዘር መዝራትና ወደ ቀጣይ የመሰብሰብ ስራ መግባት ካልተቻለ በማህበረሰቡ የሚፈጠረው ችግር ቀላል አይደለም” ብለዋል።

የክልሉ አርሶአደር በዚህ ክረምት ወደ እርሻ ካልገባ የዘር ወቅት ስለሚያልፍ በቀጣይ ገበሬው ለዓመታት ተረጂ ሆኖ የመኖር እድል እንደሚገጥመውም ነው ያወሱት።

በዚህም አሸባሪው ቡድን የዚህ ዓይነቱን ቀውስ እየፈጠረ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ “የኢትዮጵያ መንግስትና የመከላከያ ሰራዊት እዳውን እንዲሸከምለት ያደርጋል” ብለዋል ዶክተር አብርሃም

እንደርሳቸው ገለጻ ህውሃት መኖር የሚችለው የትግራይ ህዝብ ሲሞትና መከራ ሲያይ ብቻ በመሆኑ፥ መንግስትና የእርዳታ ድርጅቶች እርዳታ እንዳያደርሱ፣ ለገበሬው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዳያቀርቡ እያሰናከለ፣ ህዝብ ተራበ ብሎ ራሱ ይጮሃል።

እንዲህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ወራት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ለእርዳታ፣ ለመንግስት አገልግሎት ማስቀጠልና ለመሰረተ ልማት ግንባታ አውሏል ነው ያሉት።

ይህም በሃገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተለይ በሌሎች ክልሎች የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክልሎች ከበጀታቸው ቀንሰው የትግራይ ክልልን ለማቋቋም ድጋፍ ማድረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በቀጣይ ደግሞ ሰብዓዊ እርዳታው ወደ ሚፈለገው ቦታ ለማድረስ፣ እርሻ ሥራ እንዳያመልጥ ለማድረግ፣ የተፈናቀለውንም ተረጋግቶ ወደ የቤቱ እንዲመለስ ተጨማሪ የፖለቲካ አማራጭ በማስፈለጉ በተደጋጋሚ ከመንግስት ጋር ንግግር መደረጉን ነው ዶክተር አብርሃም የገለጹት።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ገበሬው ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለችግረኞች የሰብዓዊ ድጋፍና የእርዳታ ቁሳቁስ ለማድረስ፣ የተፈናቃዮችን ቤት ጠግኖ ወደ ቦታቸው ለመመለስ እንደሚያስችል አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በረሃ ካለው ሃይል መካከል የሰላም መንገድ የሚፈልግ መኖሩን አመላክተው፥ ለዚህ ሃይል እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

አጥፊው የህውሃት ሃይል የተበተነ ቢሆንም ለብዙ ዘመናት በክልሉ በዘረጋው የፍርሃት መዋቅር በኩል ዜጎች በማስፈራራት እንደሚገልና እንደሚያስገድልም አውስተዋል።

ለዜጎች የእርዳታ እህል እንዳይደርስ በማደናቀፍም የእርዳታ ሰራተኞችን እንደሚገድልና ዜጎች እርዳታ እንዳይቀበሉ እንደሚያስፈራራ ጠቁመው፥ ከተቀበሉ በኋላም እንዲያካፍሉት እንደሚያስገድድ አስረድተዋል፡፡

“የአጥፊው የህወሃት ቡድን ዋና አላማ ህዘቡን የጦርነት ጋሻ ማድረግ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ነገር ግን የህዝብን ጥቅም በማስቀደም የተኩስ አቁም ማድረግ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የነሱት።

አያይዘውም ሰሞኑን በተደረጉ ግጭቶች አሸባሪው የጥፋት ሃይል ይበልጥ መዳከም መቻሉ የህወሃት ርዝራዥ ሆን ብለው ህዝቡን እንዲራብ በማድረግ ለሚዲያ ፍጆታ ለማዋል እንቅስቃሴ እያደረጉ በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት የፖለቲካ መፍትሄ መውሰድ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ለትግራይ ህዝብ ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለግ ያለበት መንግስት እንጂ ለህዝቡ ግድ የሌለው የህውሃት ጥፋት ሃይል ሊሆን አይችልም” ያሉት ዶክተር አብርሃም፤ በመሆኑም መንግስት ይበልጥ ሆደ ሰፊ ሆኖ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን መስጠት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ለፌዴራል መንግስት የቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄ የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.