Fana: At a Speed of Life!

ለውጡን የሚያስቀጥል አመራር ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ብልፅግና ፓርቲ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ለውጡን ማስቀጠልና ማሻገር የሚችል አመራር ለማብቃት እየሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

በየደረጃው የሚገኙ በቁጥር 2 ሺህ የሚጠጉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት ስልጠና ነገ በአዳማ ከተማ ይጀመራል።

ሀገራዊ ሪፎርሙን ከዳር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን በፓርቲው የዴሞክራሲ ማዕከል ግንባታ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ ገልጸዋል ።

የስልጠናው ዓላማ ሀገሪቱ ያለችበትን ምዕራፍ በትክክል በመገንዘብ ለውጡን ማስቀጠልና ማሻገር የሚችል አመራር ለማብቃት ማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል።

ስልጠናው በይዘቱ የተለየ ከመሆኑም ባለፈ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የጋራ አቅጣጫና የማስፈጸሚያ ስልት የሚቀመጥበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

ሃላፊው አያይዘውም በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣ የፓርቲው መሠረታዊ መርሆች፣ ዓላማና ፕሮግራሞች በስልጠናው ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

አመራሩ ይህን ተገንዝቦ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን፣ የህዝብ ደህንነትና ልማት ማስቀጠል ብሎም ለውጡን ለማሻገር ትጥቅና ስንቅ የሚሆንለትን ግብዓት የሚያገኝበት ነው ማለታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.