Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ አራት የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 6ኛ አመት የስራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ የብድር ስምምነቶችንና አዋጆችን አጽድቋል።
የብድር ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር ያደረገቻቸው የተለያየ መጠን ያላቸው ሲሆኑ፥ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ ናቸው።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ምጣኔ ሃብት መሰረት የመጣል ፕሮጀክት፤ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝና ላልተማከለ የኤሌክትሪክና መብራት አቅርቦት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ ናቸው።
በተጨማሪም ለፍትሃዊ መሰረታዊ አገልግሎት ሁሉን አቀፍ እድገት ተጠቃሚነት መርሃ ግብር የሚውሉ ናቸው።
በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፥ የተገኙት ብድሮች ከወለድ ነጻ መሆናቸውንና ፕሮጀክቶቹን በመደገፍ ያላቸውን አስተዋጾ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የብድር ስምምነቶቹ ከኢትዮጵያ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙና ጫናቸው ያልበዛ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ላይ ተወያይቶ የቀረቡለትን አራት የብድር ስምምነቶች ረቂቅ አዋጆች አጽድቋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ቻርተርና የተባበሩት መንግስታት የመንገድ ትራፊክ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ እና የፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ አጽድቋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት በህገ-መንግስቱ የተሰጡትን ሃላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ከ20 አመታት በላይ ያስቆጠረ ክፍተቶች የሚስተዋሉበት በመሆኑ ማሻሻያ ማድረግ እንዳስፈለገ ተገልጿል።
በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አቡ ብርኪ፥ የተሻሻለው አዋጅ አሁን ያለውን የአገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አገናዝቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የፌደሬሽን ምክር ቤት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት እንዲከበር ሌሎች የተሰጡትን ተግባራት በብቃት ለማከናወን ያግዘዋል በማለት ምክር ቤቱ አጽድቆታል።
በተመሳሳይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤትን ለማቋቋም የወጣውን የማሻሻያ አዋጅም ምክር ቤቱ አፅድቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም 38 አዋጆችን ማጽደቁንና 11 ውሳኔዎችን መወሰኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.