Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ 7 ሚሊየን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም ድረስ 7 ሚሊየን ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ብሔራዊ የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
 
ኮሚሽኑ ከጥር እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የድጋፍ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎችን በጥናት መለየቱንም አስታውቋል።
 
በጥናቱ በአሁኑ ወቅት በምግብ ፍላጎት ተረጂ የሆኑት 6 ሚሊየን ሰዎች እንደሆኑና ባለፈው ዓመት ከነበረው 8 ሚሊየን ተረጂ ጋር ሲነጻጻር ቅናሽ ማሳየቱንም ሃላፊው ተናግረዋል።
 
የዚህ ምክንያት ደግሞ በመኽር ምርት የተሸፈኑ የሰብል አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች በመኽር ምርት ግኝት ለማገገም በመቻላቸው ነው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር የሚወሰነው የሰብዓዊ እርዳታና የአደጋ አይበገሬነት ሰነድ በማዘጋጀት እንደሆነም ጠቁመዋል።
 
በሀገሪቷ ከቀደመው ጊዜ በተለየ የድርቅ ክስተት እየተደጋገመ በመምጣቱ የህዝቡን አኗኗርና የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እየጎዳ መሆኑንም ተገልጿል፡፡
 
በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የአየር ንብረት መዛባት በሀገሪቷ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ ድርቁን ተደጋጋሚ አድርጎታል ነው ያሉት ሃላፊው።
 
መንግስት ጉዳቱን ለመከላከልና ለመቋቋምም ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበርና ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው ÷ ለችግሩ ወቅታዊ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎንም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር አደጋውን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ ዘላቂ የልማት ተግባራት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.