Fana: At a Speed of Life!

ለቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ዝግጅትና ተሳትፎ 1 ቢሊየን ብር የመሰብሰብ ግብ ተቀምጧል

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅትና ተሳትፎ አንድ ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ግብ መቀመጡን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገለጸ።

ኮሚቴው ዛሬ የቶኪዮ 2020 ኦሎፒክ ዝግጅትን በተመለከተ የሚጠበቁ ተግባራትን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል።

በዚሁ መሰረት ኮሚቴው የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ እንደተገለጸው፤  ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ማዋቀር፣ ገቢ ማሰባሰብ፣ ደጋፊ አባላት ማፍራት፣ ለአትሌቶች ሽኝት ማድረግና በውድድሩ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ዕቅድ ተይዟል።

ኮሚቴው ደጋፊ አባላትን በማፍራት ለኦሎምፒክ ውድድሩ ዝግጅትና ተሳትፎ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ የማሰባሰብ ዕቅድ መያዙን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል።

ገቢውን ለማሰባሰብ የታቀደው ከመንግስት፣ ከክልል ከተማ አስተዳደሮች ዝግጅትና ተሳትፎ፣ ከቴሌቶን የገቢ ማሰባሰቢያ ኘሮግራም፣ በአጭር የስልክ መልዕክት፣ ከስፖንሰር አድራጊዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቀማጭ እንደሆነ ተጠቁሟል።

እንደ ዶክተር አሸብር ገለጻ፤ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ደጋፊ አባላትን ለማፍራት ታስቧል።

በጃፓን፣ ቶኪዮ ለሚካሄደው ኦሎምፒክ የሚደረጉ ዝግጅቶችን ለማስተባበር ከተቋቋመ ብሔራዊ ኮሚቴ ባሳለፍነው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየቱም ይታወሳል።

ብሔራዊ የኦሎምፒክ ኮሚቴው በዚሁ ወቅት  ዓላማቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ለውድድር መላክ ብቻ ሳይሆን፣ በድል እንዲመለሱም ማገዝ እንደ ሆነ አስታውቀዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.