Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በ627 ሚሊየን ብር የመንገድ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ በ2012 በጀት ዓመት 43 ፕሮጀክቶችን በ627 ሚሊየን ብር እየገነባ መሆኑን አስታወቀ።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌትነት ዘውዴ እንዳሉት፥ በክልሉ ወረዳን ከወረዳ እና ዞንን ከዞን የሚያገናኙ የጠጠር መንገዶችን እንዲሁም ድልድዮችን የመገንባት ስራ እየተከናወነ ነው።

በሌላ በኩል ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ባለፉት 6 ወራት 153 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ለመገንባት አቅዶ 128 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር መገንባቱን ገልጸዋል።

ለግንባታ የሚያገለግሉ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች አለመሟላት፣ የሚሰሩ መንገዶች እና የሚያስፈልገው በጀት በወቅቱ አለመሟላት ለአፈጻጸሙ ማነስ ምክንያት መሆኑን ከአማራ ኮሙዮኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በቀጣይ ወራትም 307 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክቶችን እና 26 ድልድዮችን ለመገንባት እቅድ መያዙን ጠቅሰው፥ 43 አዳዲስ መንገዶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው አስቸጋሪ መልክዓ ምድር እና የአየር ጸባይ ባላቸው የክልሉ አካባቢዎች አዳዲስ መንገዶችን ከመገንባት በተጨማሪ ነባር መንገዶችን የመጠገን ስራም ያከናውናል ነው ያሉት።

በበበጀት አመቱ በ139 ሚሊየን 281 ሺህ 347 ብር፥ 3 ሺህ 490 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶችን የመጠገን ዕቅድ ተይዞ በስድስት ወራት ውስጥ 906 ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገን ተችሏል ብለዋል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.