Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከታገቱ ተማሪዎች ወላጆች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በቅርቡ ከታገቱት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች ጋር ተወያዩ።

በውይይቱም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተጨማሪ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተማሪዎቹ የትውልድ ቦታ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የተማሪ ወላጆች በዚህ ወቅት የልጆቻቸው አድራሻ እስከጠፋበት ዕለት ድረስ የነበራቸው የስልክ ልውውጥ ምን እንደሚመስልም ጉዳዩን በሚመለከት የተቋቋመው ግብረ-ሃይልን ለሚመሩት ኃላፊዎች አብራርተዋል።

አቶ ንጉሱ ጥላሁን ውይይቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ወላጆቹ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር በመገኘት ስለሁኔታው ተወያይተዋል።

ግብረ-ሃይሉን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በነበራቸው ቆይታም መንግስት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስፈታት እያከናወነው ያለውን ተግባር ለወላጆች በዝርዝር እንዳብራሩላቸው ነው የተናገሩት።

በውይይቱም ከወላጆች ለቀጣይ ስራ የሚሆን መረጃ መገኘቱንም ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታገቱ ተማሪዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚያሳይ የተረጋገጠ መረጃም ሆነ ማስረጃ አለመኖሩን ለወላጆቻቸው ማስረዳታቸውንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

መንግስት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ሲባል በጥንቃቄና አስተውሎት እየሰራ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ወላጆች በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ጭምር ምክክር መደረጉን ነው አቶ ንጉሱ የገለጹት።

በአጠቃላይ በመድረኩ የጸጥታ መዋቅሩና የፖለቲካ አመራሩ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ያለምንም እረፍት እየሰራ መሆኑ ተገልጾ መተማማን ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

የታገቱ ተማሪ ወላጆች በበኩላቸው መንግስት በአካል በማግኘት ስለአወያያቸው ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን ተገንዝበናል ነው ያሉት።

በውይይታቸውም መንግስት ጉዳዩን በሚመለከት እስካሁን ያከናወነውን ተግባር መረዳታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ልክ ከሰራ ልጆቻቸውን የማግኘት ተስፋቸው ትልቅ እንደሆነም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

መንግስት በቅርቡ በደምቢዶሎ አካባቢ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በመሸሽ ላይ ሳሉ የታገቱትን ለማስለቀቅ ሶስት ቡድኖችን አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.