Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ1 ሺህ 500 በላይ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጥፋት በፈፀሙ ከ1 ሺህ 500 በላይ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

እርምጃው የተወሰደባቸው ግብር ለመሰወር የሞከሩና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ሳይጠቀሙ አገልግሎት የሰጡ እንዲሁም ደረሰኝ ሳይሰጡ ክፍያ በመቀበል ጥፋት የፈጸሙ ናቸው ተብሏል።

ጥፋት በፈጸሙ ግብር ከፋዮች የገንዘብ ቅጣትና የመጨረሻ ደረጃ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን በቢሮው የግብር አወሳሰን፣ አሰባሰብና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ይታየው ፈንቴ ተናግረዋል።

እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 174 ግብር ከፋዮች ደረሰኝ ሳይሰጡ ክፍያ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙና እያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የተወሰነባቸው መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ግብር ለመሰወር የሞከሩና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ሳይጠቀሙ አገልግሎቱን ሲሰጡ የተደረሰባቸው 1 ሺህ 554 ግብር ከፋዮችም የቃልና የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የግብር ከፋዮችን የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ለማሻሻልና ፍትሃዊ የግብር አወሳሰን ስርዓት ለመዘርጋት ለግብር ከፋዮች ስለሂሳብ መመዝገቢያ ማሽን አጠቃቀም ሲሰጥ የቆየው ትምህርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.