Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት የሐሰት ወሬ ከሽንፈትና ተስፋ መቁረጥ የሚመነጭ ነው- የሥነ ልቦና ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት እያሰራጨ ያለው የሐሰት ወሬና ፕሮፓጋንዳ ከመሸነፍና ተስፋ መቁረጥ የመነጨ መሆኑን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርሲቲው የሥነ ልቦና ምሁሩ ዶክተር እዴሳ ቶሌራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ህወሓት የእውነትን አቅጣጫ በማሳት ህዝቡን በማሸበር የሥነ ልቦና ጫና ለመፍጠር እየጣረ ነው።

ቡድኑ የሀሰት ወሬና ፕሮፓጋንዳ አማራጭ መጠቀሙም ውድቀቱን ለመሸፈን ሆን ብሎ የሚያደርገው ነው ብለዋል።

በዚህም አማራጭ የትግል ስልት አድርጎ ያልያዘውን ያዝኩ በማለት ሽብር እየነዛ ህብረተሰቡ ላይ የሥነ ልቦና ጫና በመፍጠር ጥርጣሬ ውስጥ ለመክተት እየሞከረ መሆኑን ያስረዳሉ።

መንግስትና ህዝቡ ጉዳዩን እንደ ቀላል ማየት የለባቸውም ያሉት ዶክተር እዴሳ መረጃን ቀድሞ በማውጣት ይፋ ማድረግ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፤

ቀድሞ የተሰማ ወሬ በሰዎች ዘንድ ውዝግብ ስለሚፈጥር ለዚህ አጸፋ ከመስጠት ይልቅ መረጃን ለህዝበ በፍጥነት ማድረስ ይመረጣልም ነው ያሉት።

ሌላው የሥነ ልቦና ምሁር ደረጀ ኮብኮባ በበኩላቸው ሰዎች ሽንፈትን መቀበል ሲያቅታቸው በውሸት የአሸናፊነት ስሜት ያንጸባርቃሉ ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ይህን ስልት በመጠቀም ያላደረገውን አደረኩ በማለት የህዝብን ሀሳብ ለማስቀየርና ሥነ ልቦናውን ለማዳከም እየጣረ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ ከእኔ ውጭ አሸናፊ የለም የማለት እሳቤ ከምስረታው ጀምሮ ውስጡ ያለ መሆኑን ያወሱት ምሁሩ፥ ያልጠበቀው ውድቀት ከፊቱ ሲደቀን በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማሸበር ተግባር ላይ መጠመዱን አስረድተዋል።

የጀግኖች ሀገር ኢትዮጵያን ለማፍረስ አስቦ ያልተሳካለት አሸባሪው ህወሓት የሐሰት ወሬን የመንዛት ስልትን እንደ አማራጭ እየተጠቀመ መሆኑን ህዝቡ በመረዳት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሁሉም ነገር ማብቃቱን አውቆ ተስፋ የቆረጠው ቡድን የሚያሰራጨውን ውሸት ባለመስማት የደጀንነት ድጋፉን ቀጥሎ ወደ ልማት ፊቱን ማዞር አለበት ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.