Fana: At a Speed of Life!

ሳይንሳዊ ምርምሮች በአማርኛ ሊተረጎሙ ነው

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳይንስን ከቅኝ ግዛት ማውጣት የተሰኘ ፕሮጀክት አማርኛን ጨምሮ የምርምር ፅሁፎችን በስድስት የተለያዩ አፍሪካዊ ቋንቋዎች ሊተረጎሙ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአፍሪካርዚቭ ፖርታል ላይ የሚገኙ 180 የምርምር ፅሁፎችን በስድስት የተለያየ አፍሪካዊ ቋንቋዎች የመተርጎም ስራ ለመስራት ማቀዱ ተሰምቷል፡፡
አማርኛ ከሉጋንዳ ቋንቋ ጋር ሆኖ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል የተመረጠ ሲሆን÷ ከደቡባዊ አፍሪካ ኢሲዙሉ እና ሰሜናዊ ሱቱ እንዲሁም ከምዕራባዊ አፍሪካ ሀውሳ እና ዮሩባ መመረጣቸው ተመላክቷል።
አፍሪካርዚቭ ምርምራቸው ወደ እነዚህ በርካታ ሚሊየኖች ወደሚናገሯቸው ቋንቋዎች እንዲተረጎምላቸው የሚፈልጉ ፀሀፊዎችን ጥያቄ እንዲያቀርቡም መድረኩን ክፍት አድርጎ ነበር፡፡
በፕሮጀክቱ በስድስቱ ቋንቋዎች የሚሰጡ ትርጓሜዎችን በበይነ መረብ አማካኝነት ለሳይንሱ ዓለም በነፃ የማቅረብ እና ትርጓሜዎችን ተጠቅሞም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀመሮችን በማሰልጠን የትርጓሜ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማስቻል እቅድ መያዙም ነው የተነገረው፡፡
ፕሮጀክቱ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ባሉ መንግስታትና ግለሰቦች እንዲሁም ጎግል ኩባንያ ድጋፍ ተደርጎለት ሥራውን በይፋ የጀመረው፡፡
በዋናነት ቋንቋዎቹ በዲጂታሉ ዓለም ቦታ እንዲኖራቸው ማስቻልን ያለመ መሆኑን ኔቸርን ጠቅሶ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ገልጿል፡፡
ትርጓሜ የሚሰጥባቸው ጥናታዊ ፅሁፎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶች ውስጥ ያሉ በርካታ ዘርፎችን የሚዳስሱ እንደሚሆኑም ተመላክቷል፡፡
በትርጉም ስራ ወቅት በቋንቋዎቹ ውስጥ አቻ ፍቺ የሌላቸው ቃላት ሲገኙ የቃላት ፍቺ እና የሳይንስ ተግባቦት ባለሙያዎች ትርጓሜ እንዲያፈላልጉላቸው በማድረግ አዳዲስ ፍቺዎችን ለማግኘትም ታስቧል፡፡
ሳይንስን በራስ ቋንቋ አለመማር በአፍሪካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በተለይም የትምህርት ተቋማት ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሾች እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይ ሳይንስን ከቅኝ ግዛት ማውጣት ‘ዲኮሎናይዝ ሳይንስ’ የትርጉም ስራውን በወራት ውስጥ አጠናቆ በ2014 ዓ.ም ሲያቀርብ ችግሩን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.