Fana: At a Speed of Life!

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ 726 ተማሪዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ለ13ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 5 ሺህ 726 ተማሪዎች አስመረቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ፥ በዋናው ግቢ ፣ በኦቶና ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል እንዲሁም በታርጫ ግቢ በመደበኛ፣ በሳምንት መጨረሻ ቀናትና በምሽት መርሐ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 304 ወንድና 1 ሺህ 964 ሴት ተማሪዎች ይመረቃሉ ብለዋል።

እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር 385 ወንድና 63 ሴቶችን ሲያስመርቅ በሶስተኛ ዲግሪ ስድስት ወንድና አንድ ሴት እጩ ዶክተሮችን አስመርቋል ነው ያሉት።

ዩኒቨርሲቲው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ ከ500 ሺህ በላይ ችግኝ በማፍላት ደማቅ አሻራ ማሰረፉንም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የሃገሪቱን ሰላም እያስከበረ በዱር በገደሉ ለሚዋደቀው የሀገር መከላከያ ሠራዊት 100 ኩንታል ጤፍ፣ 2 ሚሊየን ብር በገንዘብ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የወር ደመወዝን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረጉንም አውስተዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ እንደሀገር ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግስት በልዩ ትኩረት ለሀገር ለውጥና እድገት እየተጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ተስፋ ለጣለችባቸው ውድ ሀገራቸው በታማኝነት እንዲያገለግሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ከተመራቂዎች ውስጥ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 185 ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚቀሩ ተገልጿል።

በአበበች ኬሻሞ እና በመለሰ ታደለ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.