Fana: At a Speed of Life!

አይነ ሰውር አዛውንትና ህጻናትን የሚገለውን ሰርጎ ገብ ቡድን ካለበት እንዳይወጣ በጋራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)አይነ ሰውር፣ አዛውንትና ህጻናትን የሚገለውን ሰርጎ ገብ አሸባሪ ቡድን ካለበት እንዳይወጣ በማድረግ እዛው ለመቅበር ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ሲሉ የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በሬዎቻችን ለሚገል ልጆቻችንን እና ሚስቶቻችንን ለሚያጠፋ የጁንታ ቡድን መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ የጋዜጠኞች ቡድን በሰሜን ወሎ ባደረገው ቅኝት ያነጋገራቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች አካባቢያቸውን ላለማስደፈር በንቃት እየጠበቁ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በወሎ ግንባር የሚገኙት አርሶ አደሮቹ አይነ ሰውር አዛውንትና ህጻናት የሚገለውን ወራሪ ባንዳ አይቀጡ ቅጣት እያደረሱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ጁንታው ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ እያደረገ ቢሆንም በተደጋጋሚ እየተደበደበ እየተመለሰ ነው ብለዋል፡፡

ሰርጎ ገቡ ቡድን ካለበት እንዳይወጣ በማድረግ እዛው ለመቅበር ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን ገለጸዋል፡፡

ነዎሪዎቹ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ የጸጥታ ሀይሎች በአካባቢው ከመድረሳቸው በፊት ጁንታው ጋር ፊት ለፊት በመተናነቅ ስርጎ ገቡ ወራሪ ባለበት እንዲወሰን አሰገድደውታል፡፡

በቦታው ያገኘናቸው አርሶ አደር ሰይድ መሀመድ እና አርሶ አደር ሰይድ አብዱ እንደነገሩን ወራሪው ሀይል በወገናችን እና በሀገራችን ላይ አየፈጸመ ያለውን ግፍ እና በደል በአካባቢያቸው ለመድገም ጥረት ያደረገውን ጁንታ ቡድን ለቀናት በመፋለም በቆረጣ ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች ለመሰፋፋት የነበረውን ቅዥት ማምከናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ወሎአርሶ አደሮቹ ሴትን ለሚደፍር ሀብትን ለሚያወድም፣ ሀገርን ለሚዘርፍ አጥፊ ቡድን እሰኪጠፋና እሰኪቀበር ቀንና ሌሊት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህም ከመከላከያ ከአማራ ልዩ ሀይልና የሚሊሻ አባላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በወሎ ግንባር ያለው የመከላከያ ሰራዊት አመራር የአከባቢው ማህበረሰብ ጁንታው እንዳይስፋፋ የመከቱበትና የገደቡበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጁንታው በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ካለበት ሳይወጣ ታሪክ ይሆናል ያሉ ሲሆን÷ የማህበረሰቡ ድጋፍም ለዚህ ድል ትልቅ መሠረት ይሆናል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.