Fana: At a Speed of Life!

ያለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለኢትዮጵያ ህልውና በጋራ መቆም አለብን-ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎች ያለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለኢትዮጵያ ህልውና በጋራ መቆም እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥሪ አቅርበዋል።

 
የኢዜማ ፓርቲ አመራርና አባላት “ደሜን ለእናት ሀገሬ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘት ደም ለግሰዋል።
 
የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የደም ልገሳ መርሃ-ግብሩ የተዘጋጀው ፓርቲው ለሀገሩ ህልውና መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ለህልውና ዘመቻው የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ ወደ ግንባር እስከመዝመት የደረሰ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
 
ፓርቲው የአሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች የ250 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል።
 
የሀገርን ህልውና ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ ያለምንም የፖለቲካ ልዩነት ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ በጋራ መቆም እንዳለበት ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው የፓርቲው አመራሮች ግንባር ድረስ በመሄድ ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።
 
በሽብር ቡድኑ ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች የአልባሳት ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ነው የተናገሩት።
 
የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 9 የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ በሀይሉ ደመሳ ናቸው፡፡
 
ኢትዮጵያውያን “ኢትዮጵያን ለማዳን የትም፣ መቼም በምንም” በሚል ለቀረበላቸው ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ለሀገራቸው ህልውና መጠበቅ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እያደረጉ ነው።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.