Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል ህወሓት እና ሸኔን የሚያወግዝ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል የአሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን ጥምረት የሚያወግዝና የሃገርን ህልውና ለማስጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘውን መከላከያ ሠራዊት የሚደግፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ከክልሉ የከተማና የገጠር ወረዳዎች የተውጣጡ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በሰልፉ የሃገርን አንድነት ለመናድና ሃገር ለማፍረስ ያልተቀደሰ ጋብቻ የፈጸሙትን አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን የሚያወግዙ የተለያዩ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ለአብነትም ትህነግና ሸኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ናቸው፣ የሸኔና የትህነግ ኃይሎች በሃገራችን ላይ እየፈጸሙት ያለውን ተግባር እናወግዛለን፣ የሃገራችንን ሉዓላዊነት ለድርድር አቅርበን እንደማናውቅ ታሪካችን ይመሰክራል፣ ህውሓትና ሸኔ የኢትዮጵያ ነቀርሳ ናቸው፣ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ የለም፣ ምዕራባውያን ኃይሎች በእጅ አዙር ሃገራችንን ማንበርከክ አይችሉም የሚሉ ሃሳቦች ተስተጋብተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ÷ አሸባሪው ህወሓት ሃገር ለማፍረስ የጀመረውን ጥረት ለመቀልበስ ህዝቡ እያሳየ ያለው ተነሳሽነትና ድጋፍ የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ህወሓትና ተላላኪው ሸኔ የፈጠሩት ያልተቀደሰ ጋብቻ በህዝቦች የጋራ ጥረት ውጤታማ አይሆንም ያሉት ወ/ሮ ሚስራ ÷ ህልውናን ለማስጠበቅ ከሚደረገው ዘመቻ ጎን ለጎን በኢኮኖሚያዊ አሻጥር ችግር ለመፍጠር በሚጥሩ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጠዋል፡፡
የሰልፉ ተሳፊዎች በበኩላቸው÷ መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለውን የህልውና ዘመቻ በድል እስከሚያጠናቅቅ ድረስ አጋርነታቸውንና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በተሾመ ኃይሉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.