Fana: At a Speed of Life!

የሕልውና ዘመቻውን በቴክኖሎጂ እንደግፋለን – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ወታደራዊ መሣሪያዎችን በመጠገንና ቴክኖሎጂያዊ ድጋፎችን በማድረግ የህልውና ዘመቻውን እንደሚደግፉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የመንግስት፣ የግል ኮሌጅ እና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምሁራን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ “ሀገርን የማፍረስ አጀንዳ በማስቀልበስ ኢትዮጵያን የማዳን ሀላፊነት እንወጣለን” በሚል ሀሳብ በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ የመንግስት፣ የግል ኮሌጅ እና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምሁራን የሚሳተፉበት የማጠቃለያ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተሳተፉት ምሁራን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጫናዎችን በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በምሁራዊ ውይይቶች በመሳተፍ ለመመከትና የሕልውና ዘመቻው ደጀን ለመሆን መነሳታቸውን ነው የገለጹት።

አሸባሪው ህወሓትና የቡድኑ ደጋፊዎች የሚያሰራጩትን የተሳሳተ መረጃ በማጋለጥ እና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን በመከላከልም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩም ጠቁመዋል።

በተለይም ዘርፉ ያለውን የቴክኒክ አቅም በመጠቀም ወታደራዊ መሣሪያዎችን በመጠገንና ቴክኖሎጂያዊ ድጋፎችን በማድረግ የህልውና ዘመቻውን በሙያቸው እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

በተሠማሩበት የስራ ዘርፍም ታታሪና ሀገር ወዳድ ዜጎችን በማሰልጠን ለሃገር ዘብ የሚቆሙ ዜጎችን ለማፍራት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በበኩላቸው÷ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት፣ የግል ኮሌጅ እና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ህወሓትና ሌሎች የቡድኑ ደጋፊዎች ኢትዮጵያ ላይ የደቀኑትን የህልውና አደጋ ለመመከት የተጠናከረ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

የሽብር ቡድኑን በማጥፋት በአጭር ጊዜ ወደ ልማት ለመመለስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከመንግሥትና የጸጥታ ሀይሉ ጎን በመቆም እንደሚሰሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.