Fana: At a Speed of Life!

የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስቆም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቀነስ የሚያስችል በተመረጡ ሁለት ዞኖች ተግባራዊ የሚሆን ሺ ትራይቭስ የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር እና በደቡብ ክልል ደግሞ ጌዲኦ ዞኖች የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቀነስ በኢኮኖሚ አማራጭ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው ዛሬ ይፋ የተደረገው፡፡
ፕሮጀክቱን ከኬር ኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር እንዲሁም የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለስራው መሳካት በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚነስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ፥ በኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች እያደገ የመጣውን የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ለመቅረፍ ከመንግስት ስራዎች በተጨማሪ አጋር ድርጅቶች ጋር መስራት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡
በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ሁኔታዎች ቁጥጥር፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ይልማ፥ በ2025 ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች አካል የሆነውን የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቆም ለሚለው እቅድ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የኬር ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ዳይሬክተር ካትሊን ጎጊን፥ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ስራ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ተከታታይ ስራዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኬር ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የሰራተኛ ዲፓርትመንት ባገኘው 225 ሚሊየን ብር የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት 10 ሺህ 300 ግለሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ፕሮጀክቱ እናቶች የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ በማድረግ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ማስቻልን ያለመ ሲሆን በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.