Fana: At a Speed of Life!

ፈረንሳይ ለአፍሪካ 10 ሚሊየን ዶዝ የኮሮናቫይረስ ክትባት ድጋፍ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ 10 ሚሊየን ዶዝ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለአፍሪካ ለማቅረብ ከአፍሪካ አጋር አካላት ጋር እየሰራች መሆኑን የአፍሪካ የበሽታዎች መካለከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) አስታወቀ፡፡

የአፍሪካ ህብረት እና የፈረንሳይ መንግስት አዲስ በተፈራረሙት የአጋርነት ማዕቀፍ መሰረት የህብረቱ አባል ሀገራት በመጪዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ 10 ሚሊየን የአስትራ ዜኔካ እና የፋይዘር ክትባቶችን እንደሚያገኙ ሲዲሲ አፍሪካ ገልጿል፡፡

በተያዘው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ፈረንሳይ ከአፍሪካ የክትባት አፈላላጊ ጥምረት ጋር በገባቸው አዲስ የአጋርነት ስምምነት መሰረት ክትባቱን በሲ ኢ ፒ አይ፣ በጋቪ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በዩኒሴፍ በኩል ለአፍሪካ በመለገስ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን መረጃው አስታውሷል፡፡

የአፍሪካ የክትባት አፈላላጊ ትብብር ተነሳሽነት የአፍሪካ ሀገራት የሚስፈልጋቸውን የክትባት መጠን 50 በመቶ የሚሆነውን በግዢ ቀሪውን ደግሞ ከኮቫክስ ጋር በመተባበር በድጋፍ የሚገኝበትን ስርዓት ዘርግቶ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡

በጥረቱ እስካሁን ድረስ ከ400 ሚሊየን ማለትም ለአህጉሩ 1/3 ህዝብ ክትባቱን ተደራሽ ያደረገ ሲሆን÷ ከመስከረም ወር ጀምሮ ለክትባት ግዢ የሚውል የ3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ከዓለም ባንክ ጋር ስምምነት ማድረጉም ተገልጿል፡፡

ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ክትባቱ ለአፍሪካ አህጉር በፍትሃዊነት እንዲዳረስ ልዩ ልዩ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው ፈረንሳይ በዓለም ጤና ድርጅት በኩልም አህጉሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረጓ ተጠቅሷል፡፡

የፈረንሳይ መንግስት ከአፍሪካ ጋር ባለው የአጋርነት ስምምነት መሰረት የተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የሚያደርገውን የክትባት ድጋፍ እስከ 60 ሚሊየን እንደሚያደርስ ተነግሯል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.