Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጫናን ለመቋቋም የውስጥ ትብብርና አንድነታችን መጠናከር አለበት- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ለመቋቋም የውስጥ ትብብርና አንድነታችን ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

አሸባሪው ህውሓት አገር ለማፍረስ የኢትዮጵያን ጠባቂና ጠበቃ ሰራዊትን ድንገት ከመውጋት ጀምሮ እስካሁንም ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለ የህዝብና የመንግስት ንብረት እያወደመ ጥፋቱን ቀጥሏል።

በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ የፈፀመውን የጭካኔ ድርጊት ተከትሎ መንግስት አገር የማዳን ዘመቻ ውስጥ ገብቶ በአጭር ጊዜ አጠናቀቀ።

በመቀጠልም ትግራይን መልሶ የመገንባት፣ የጁንታውን መሪዎች የማደንና ወደ ህግ የማቅረብ ተግባር ሲከናወን ቆይቶ ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ በመስጠት ሰራዊቱ አካባቢውን ለቅቆ ወጥቷል።

አሸባሪው ህወሓት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ከየዋሻው በመጠራቀም በአማራና አፋር ክልሎች ሰርጎ በመግባት ሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል ከማድረግ በተጨማሪ በንፁሃን ላይ በርካታ ጥፋቶችን እያደረሰ ይገኛል።

በመሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ እያለ ሚዛናዊነት የጎደላቸው አሜሪካና ምእራባዊያን የኢትዮጵያን መንግስት ጥረት “ባላየ” በማለፍ ከአሸባሪው ጋር ድርድር የሚል ፍርደ ገምድልነት ይዘው ጫና እያሳደሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል።

ከመንግስታቱ ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል አገራት ሩሲያ እና ቻይና ለፍትህና እውነት በመቆማቸው የኢትዮጵያን መንግስት ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል የሚል አቋም ማራመዳቸውን ጠቅሰዋል።

ከተለዋጭ አባላትም ኬኒያ እና ህንድ ተመሳሳይ አቋም ማራመዳቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ ፍርደ ገምድሎችን ታዝበናል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ለመቋቋም የወዳጅ አገራት ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር በጋራ መቆም አለብን ነው ያሉት።

የውጭ ሃይሎች በመካከላችን ክፍተት ካላገኙና በጋራ ከመከትናቸው የሚያደርሱብንን ጫና መቋቋም እንችላለን ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የውስጥትብብራችን ይጠናከር፤ አሸባሪና ከሃዲዎችንም በጋራ እንመክት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያዊያን በቴክኖሎጂውም ይሁን በየትኛውም አውደ ግንባር በንቃት በመሰለፍ ለአገራቸው ህልውና በጋራ መሰለፍ አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.