Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኡጋንዳና ሩዋንዳ ጉብኝት ውጤታማ ነበር-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ አህመድ የኡጋንዳና ሩዋንዳ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከአገራቱ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር ረገድ ውጤታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች ያደረጉት የሥራ ጉብኝት ውጤማ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቆይታቸውም ከአገራቱ መሪዎች ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መመክራቸውን ተናግረዋል።

አገራቱ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት በጋራ መፍታት እንዳለባቸው መወያየታቸውን ጠቁመው፥  ጉብኝቱ “ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክሮታል” ብለዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያን አቋም ማንጸባረቁን አስታውሰዋል።

በተለይም አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል አመልክተው፥ በአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ላይም ጣልቃ መግባት እንደማያስፈልግ በግልጽ መናገራቸውን አውስተዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የዚህ ሁሉ ችግር አሸባሪው የህወሓት ቡድን መሆኑን አገራቱ እውቅና መስጠታቸውን  ገልጸው፥ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔም በአዎንታ ተመልክተውታል ነው ያሉት።

እነዚህም አገራት ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን መንግሥት በአድናቆት እንደሚመለከተው ገልጸው፥ አሁንም አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ሆኖም አሁንም በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ያልተረዱ በተቃራኒው የተሰለፉ አገራት መኖራቸውን ጠቁመው፥ እነዚህንም አገራት ለማስረዳት “ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ይጠናከራሉ” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው፥ ለዚህም በመንግሥት የተካሄዱ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ጎን ለጎንም በኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚካሄደው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን እየያዘ ለመጣው አዎንታዊ አቋም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

ዜጎች በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም ያስተዋወቁበትም ጥረት ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም ሚኒስቴሩ አሁን ላይ መደበኛውን የዲፕሎማሲ ሥራ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጋር በማጣመር ለተሻለ ውጤት መትጋት በሚያስችለው ቁመና ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.