Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት ያሰለፋቸው የትግራይ ወጣቶች የጥፋቱ ተባባሪ እንዳይሆኑ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚል አሸባሪው ህወሃት ለጦርነት ያሰለፋቸው የትግራይ ወጣቶች የጥፋቱ ተባባሪ እንዳይሆኑ ተጠየቀ።

አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ በማለት ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ጠላቶች ጋር ተባብሮ የማይሳካ ትግል እያደረገ ነው።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ፥አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ቅዠቱን እውን ለማድረግ የትግራይ ህፃናትን ወደ ጦርነት እየማገደ ነው ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ታዳጊዎችን በጦርነት እያስጨረሰ የትግራይ እናቶች የወላድ መካን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ለራሱ ጥቅም እስካስገኘለት ድረስ የትግራይ እናቶችንም ሆነ ህፃናትን የማይምር አረመኔ ቡድን መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

በመሆኑም አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት ያሰለፋቸው የትግራይ ወጣቶች የጥፋቱ ተባባሪ መሆን የለባቸውም ሲሉ ዶክተር አለሙ ስሜ አስታውቀዋል ።

ቡድኑ ባለፈው ጥቅምት ወር ራሱ በለኮሰው እሳት መለብለቡን አስታውሰው ፥የመንግስትን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ ለእኩይ ዓላማው በመጠቀም የትግራይ እናቶችን ዘር እንዳይኖራቸው እያደረገ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የትግራይ ወጣቶች ከቻሉ የሽብር ቡድኑን በመዋጋት ካልቻሉ ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራና አፋር ልዩ ሃይሎችና ሚሊሻዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የወሎ ግንባር የህዝብ ንቅናቄ ሃላፊ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ በበኩላቸው፥ የሽብር ቡድኑ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ወግ ያፈነገጠ አስተሳሰብ የሚከተል እምነት የሌለው ቡድን ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ ታሪካዊውን የጨጨሆ መድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሳሪያ አውድሟል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ በመከፋፈል እርስ በእርሱ በማባላት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረው ሴራ በፈለገው ልክ ባይሄድም እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ከንቱ ቡድኖችን አላጣም ብለዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመዝመት የአሸባሪውን ቡድን እየተፋለመ መሆኑን አንስተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚኖርበት ምንም አይነት አመክንዮ የለም የሚሉት አቶ ወንዳለ፥ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ ስሙ ከመቃብር በላይ እንዳይነሳ ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.