Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ቀንድና በአፍሪካ ለሚኖር ሰላምና እድገት አሜሪካ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን ማሳየት እንዳለባት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) እስትራቴጂካዊ አካባቢ በሆነው የአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአፍሪካ ለሚኖር ሰላምና እድገት አሜሪካ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን ማሳየት እንዳለባት የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደብዳቤ አስገብቷል።

በደብዳቤው አሁን በኢትዮጵያ ለሚታዩ ችግር ያለፉትን ሰላሳ ዓመታት የፖለቲካውን ሂደት ማወቅ ያስፈልጋል ብሏል።

በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች በመካከላቸው ቅራኔና መለያየት እንዲፈጠር መሠራቱን አመላክቷል።

አሸባሪው ሕወሓት ይመራው በነበረው መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የህዝብ ሀብት ዝርፊያ እና በመንግስታዊ የሽብር ወንጀሎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በጋዜጠኞችና በግለሰቦች ላይ ሲፈጸም ነበር ብሏል።

ህወሓት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ሰላማዊ መንገድን መምረጥ ትቶ ወደ ጦርነት መግባቱን አስታውሷል።

ባለፉት ሦስት አመታት የነበረ መዋቅሩን በመጠቀም ግጭቶች እንዲከሰቱ፣ ዜጎች ለሞት እንዲዳረጉና በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን መስራቱን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ደግሞ በሃገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የፌደራል መንግስቱን በሀይል ከስልጣን ለማስወገድ ወደ እንቅስቃሴ መግባቱን አስታውቋል።

መንግስት ይህንን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱንና በመቀጠልም ለዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የእርሻ ስራዎች እንዲሰሩ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሷል።

አሸባሪው ህወሓት ግን ህጻናትን ለጦር በማሰለፍ ጭምር ወደ አጎራባች ክልሎች ጥቃት መሠንዘሩን በመጥቀስ፥ በአፋርና በአማራ ክልሎች ንጹሃን ላይ ጭፍጨፍ በማካሄድ ንብረት በማውደም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ማፈናቀሉን ነው ያመለከተው።

አሜሪካም በእነዚህ ክልሎች የሚኖሩ ተፈናቃዮችን በመደገፍ አጋርነቷን እንድታሳይና ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ገለልተኛ በመሆን ድጋፏን እንድትሰጥ ጠይቋል።

በዮኔስኮ የተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶች ደህንነትና የህወሓት የውድመት አካሄድ እንደሚያሳስበውም አመልክቷል።

የአሜሪካ መንግስት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነት በመረዳት ለአንድ ወገን ያደላ እይታውን እንዲያስተካክልና ይህንንም የሚያሰራጩ ዓለም ቀፍ ሚዲያዎች እርምት እንዲሰጡ አሳስቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.