Fana: At a Speed of Life!

ዜጎች ደም ለመለገስ ያሳዩት ፈቃደኝነት ደም የመለገስ ታሪክን የለወጠ ነው – ብሄራዊ የደም ባንከ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎች ደም ለመለገስ እያሳዩ ያለው ፈቃደኝነት በኢትዮጵያ የደም ልገሳን ታሪክ የለወጠና ያሳደገ መሆኑን ብሄራዊ የደም ባንከ አገልግሎት ገለጸ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የደም ባንከ አገልገሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ እንዳሉት÷ አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ከፍተኛው የደም መጠን እንዲሰበሰብ ምክንያት ሆኗል።

ይህን ተከትሎም በህዳር ወር 2013 ዓ.ም ብቻ ከዚህ ቀደም በዓመት ይሰበሰብ የነበረውን ያህል የደም መጠን ማለትም 38 ሺህ ከረጢት ደም ለመሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት።

ከህዳሩ ልገሳ በኋላም የቀጠለው የደም ልገሳ ተግባር በተለይ ከሀምሌ እስከ ነሐሴ ዜጎች ያለማቋረጥ በከፍተኛ ደረጃና ዓይነት ደም የለገሱበት ወቅት ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል።

ከዚያ በኋላም የታየው ለውጥ ተቋሙ በጎ ፈቃደኞች ደም እንዲለግሱ ከማግባባት የተሻገሩ ሌሎች የአገልግሎት ስራዎቹ ላይ እንዲያተኩር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው ልምድ ዜጎች የሆነ አጋጣሚን መነሻ በማድረግ አንድ ጊዜ ደም ከለገሱ በኋላ ተመልሶ ለመምጣት ዓመታትን ይፈጅባቸው እንደነበርም ነው አቶ ያረጋል ያነሱት።

ዛሬ ላይ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ህልውና የቆሙ ዜጎች በፈቃደኝነት ደም በመለገስ ላይ በመሆናቸው የነበረው ልማድ መቀየሩን፣ የደም ለጋሹ ቁጥር መጨመሩንና የሚለገሰው የደም መጠንም በእጅጉ ማደጉን ነው የሚገልጹት።

አንድ ሰው በሚለግሰው ደም የሶስት ሰዎችን ህይወት ማዳን እንደሚቻል ይታወቃል።

በትእግስት አብርሀም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.