Fana: At a Speed of Life!

የተጣለብንን ህዝባዊ አደራ ለመወጣት ህይወታችን እስከመስጠት ቁርጠኞች ነን-የአፋር ክልል ም/ቤት አባላት

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጣለብንን ህዝባዊና ሀገራዊ አደራ በብቃት ለመወጣት ደም ከመለገስ ጀምሮ ህይወታችንን እስከመስጠት ድረስ ቁርጠኞች ነን ሲሉ የአፋር ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
 
የምክር ቤቱ አባላት  ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች ጸጥታ ኃይሎች ደም ለግሰዋል።
 
የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ እንደተናገሩት÷ ሀገርን ለማዳን የሀገር መከላከያን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም የጸጥታ መዋቅር እየተዋደቁ ይገኛሉ።
 
በሃይል ሊጨፈልቀን የመጣውን ወራሪ አሳፍሮ በመመለስ ታሪካዊ ሃላፊነቱን መወጣት የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመቆም በገንዘቡ፣ጉልበቱና እውቀቱ የጀመረውን ደጀንነት ድጋፍ በማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል።
 
ለጸጥታ መዋቅሩ ያለንን አጋርነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማቀላጠፍ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከፊት ወጥተን ህዝቡን መምራትና በተግባርም አርአያ ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል ብለዋል።
 
በዚህም እሳቸውን ጨምረው የምክር ቤቱ አባላት የተጣለባቸውን ህዝባዊና ሀገራዊ አደራ በብቃት ለመወጣት ደም ከመለገስ ጀምሮ ህይወታቸውን እስከመስጠት ድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
 
ህብረተሰቡ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ በሁለንተናዊ መልኩ እያደረገ የሚገኘውን ንቁ ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
የምክር ቤቱ አባል አቶ አሊ ሁሴን በበኩላቸው÷ የጥፋት ቡድኑ ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ የአፋር ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
 
እሳቸውም ህይወታቸውን እየሰጡ ለሚገኙት ጀግኖች ደም መለገስ ብቻ በቂ ባለመሆኑ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ነው ያሉት።
 
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በ”ጋሊኮማ ” የንጹሃን አርብቶ አደሮች ላይ የፈጸመውን የግፍ ጭፍጨፋ ያወሱት ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ አህመድ ሃይሰማሌ÷የጥፋት ቡድኑን ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማ ለማምከን የአፋር አርብቶ አደር ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የህይወት ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የጥፋት ቡድኑ ጨርሶ እስከሚደመሰስ ድረስ ለሀገር ክብር መስዋዕትነቱ እንደሚቀጥልና እሳቸውም እንደ አመራር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ሶሰተኛ ቀኑን የያዘውና ዛሬ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የክልሉ ምክር ቤቱ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በመወያየት ላይ ይገኛል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.