Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ጎንደር ዞን የጠላት ሀይል ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነው

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ጎንደር ዞን የጠላት ሀይል ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለፀ።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ የህወሓት አሸባሪ ሀይል በሶስት አቅጣጫ ወደ ደባርቅና ዳባት ዋና መስመር ለመግባት እየተፍጨረጨረ ይገኛል።

በተለይ ጭና በተባለው ቦታ በኩል ጠላት ዋናውን መንገድ ለመቁረጥ አላማ አድርጎ ቢንቀሳቀስም በወገን ሀይል እየተደመሰሰ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ የአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና የዞኑ ነዋሪዎች በቅንጅት የጠላትን የክፋት ጉዞ በተባበረ ክንድ እየመከቱና በብዛት የመጣውን ጠላት እየደመሰሱ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የወገን ሀይል በወሰደው የማጥቃት እርምጃም የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

አጥፍቶ ለመጥፋት የቆረጠው ጠላት ወደ ደባርቅና ዳባት መስመር የጀመረው የጥፋት ጉዞ ቢገታም፥ አሁንም በዞኑ ልዩ ልዩ ቦታዎች ተበትኖ የሚገኝ በመሆኑ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

የዳባት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰውነት ውባለም በበኩላቸው፥ በወቅን ተራሮች ግርጌ ታላቅ ጀብዱ መፈፀሙን ጠቁመዋል።
የወቅን ተራሮችን ለመያዝ አሰፍስፎ የመጣው ሀይል አይቀጡ ቅጣት መቀጣቱን ጠቁመው፥ ግማሹ ሲደመሰስ የተቀረው መውጫ አጥቶ እየፈረጠጠ ነው ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዮ ሀይል እና ፋኖ የፈፀሙት ጀብዱ አስደናቂ ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪው ከግንባር በስልክ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በቆላማው የዳባት ወረዳ ክፍል ተመቶ ወደ ደጋማው ክፍል ተሰባስቦ የነበረው አሸባሪ ቡድን በተባበረ ክንድ ተመቶ መግቢያ አጥቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የፈረጠጠውን ሀይል የአካባቢው ማህበረሰብ ተከታትሎ እርምጃ እንዲወስድበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በነብዩ ዮሐንስ እና ክብረወሰን ኑሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.