Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ከ30 በላይ ምዕመናንን ገድሎብናል – መላእከ ሠላም መርጌታ ሙሴ ህሩይ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ከ30 በላይ ምዕመናንን መግደላቸውን እና በጾመ ፍልሰታ ስጋ እንዲበሉና ወተት እንዲጠጡ ማስገደዳቸውን መላእከ ሠላም መርጌታ ሙሴ ህሩይ የጋሰይ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡

የአሸበሪው ህወሓት ታጣቂዎች በጋይንት ወረዳ የጋሳይ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አጥቢያ ተገልጋይ የሆኑ ከ30 በላይ ምእመናን መግደሉ ሳያንሰው ምዕመናኑን በጾመ ፍልሰታ አስገድዶ ወተት እንዲጠጡና ስጋ እንዲበሉ በማድረግ ሀይማኖታዊ በደል ፈጽሞብናል ሲሉ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እንደተናገሩት÷ ታጣቂዎቹ ከ30 በላይ የጋሰይ ዙሪያ የደብሩ አጥቢያ ምዕመናንን ገድለዋል።

ቅዳሴ ላይ የነበሩ ሶስት የደብሩ አገልጋዮችም ቆስለው የተወሰኑት በህክምና ላይ ሲሆኑ÷ ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በታጣቂዎች በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ግድግዳና መስኮቶቹ ላይ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።

በደብሩ አጥቢያ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ ከ30 በላይ ምዕመናን በአሸባሪው ህወሓት በመገደላቸው የፍልሰታ የሱባዔ አገልግሎት በቤተክርስቲያኑ ተቋርጦ እንደነበር አስታውቀዋል።

ታጣቂዎቹ በጾም ወቅት ክርስቲያኖችን እያስገደዱ ምዕመናኑን ወተት እንዲጠጡና ስጋም እንዲበሉ ያስገድዱ እንደነበርም አውስተዋል።

ይህም ከሁሉም በደል የከፋ ሀይማኖታዊ በደል ነው ያሉት የደብሩ አስተዳዳሪ÷ ምእመኑ ከእምነቱ እንዲጣላ፣ አንገታቸውን እንዲደፋ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ውርደት ለማድረስ አቅደው መስራታቸውን ጠቁመዋል።

በቅዳሴ ወቅት አሸባሪው ህወሓት በደብሩ ግቢ ውስጥ በጣለው የከባድ ጦር መሳሪያ ምክንያት የመቁሰል አደጋ የደረሰበት ዲያቆን ሳሙኤል ኢያሱ እንደሚለው÷ በወቅቱ እሱን ጨምሮ ሶስት አገልጋዮች የቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ እንደነበሩና በወደቀው የከባድ መሳሪያ ፍንጥርጣሪ እርሱ ጉልበቱ ላይ ሌሎች ደግሞ እጃቸውና ትከሻቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ህክምና እየተከተተሉ እንዳሉ ዲያቆን ሳሙኤል ተናግሯል፡፡

አሸባሪው ቤተ ክርስቲያንን እንዲህ መዳፈሩ ጸረ ሀይማኖት፣ ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝብ እንደሆነና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ሊያጠፋው እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

በአሸባሪው ከተገደሉት ምዕመናን ውስጥ የደብሩ አስተዳዳሪ እናት አንዷ ስለመሆናቸውም መገለጹን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.