Fana: At a Speed of Life!

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች አሸባሪው ትህነግ ጋር እየተፋለሙ ለሚገኙት መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይሎችና ሚኒሻዎች ደም ለገሱ፡፡
 
በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ÷ የረጅም ዘመን ሃገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተለያዩ መንገዶች ተሞክሮ ባለመሳካቱ በአሁኑ ወቅት በግልጽ ጦርነት እንደተከፈተባት ተናግረዋል፡፡
 
ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ አመራሮችና ሠራተኞች ለሀገራቸው ሕልውና በግንባር እየተፋለሙ ለሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ልዩ ኃይሎችና ሚኒሻዎች የምትለግሱት ደም ትልቅ ዋጋ ያለው ነው ብለዋል፡፡
 
ወቅቱ የሀገሪቱን ሕልውና ለማፍረስ ግልጽ የሆነ ጦርነት የተከፈተበት መሆኑን ጠቁመው ዋጋ ከፍሎ ሀገርን ማሻገር ተገቢና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
 
በትግራይ ውስጥ ጁንታው ያፈረሳቸውን የኤሌክትሪክ፣ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ብዙ ጥረት መደረጉንንም ተናግረዋል፡፡
 
በመልሶ ግንባታው ወቅትም ብዙ ሠራተኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሰዋል፡፡
 
ሁንም በተሰጠው የጽሞና ጊዜ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ዘልቆ በመግባት ጁንታው ብዙ መሠረተ ልማቶችን ማውደሙን ገልጸው÷ የወደመውንም መልሶ ለመገንባት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
 
በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎችም የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ለመሥራት ባለሙያዎች ወደ ስፍራዎቹ ተጉዞው የልየታ ሥራ እንደተሠራ ጠቁመዋል፡፡
 
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ አመራሮችና ሠራተኞች ቀደም ብሎ ቃል በተገባው መሠረት በአጠቃላይ 109 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር መሠባሰሰቡንና ወደሚመለከተው አካል ገንዘቡ እንዲተላለፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ መጻፉንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
 
በደም ልገሳ መርሐ ግብሩ ላይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተጨማሪ የመስኖ ልማት ኮሚሽን፣ የውሃ ልማት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የውሃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተው ደም መለገሳቸውን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.