Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል የሚስተዋለው የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) በሀረሪ ክልል በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየተባባሰ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ የጤና ቢሮ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ግባችንን እናሳካለን በሚል መሪ ቃል 2013 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከሚመከለታቸው አካላት ጋር እየተወያየ ነው፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም መድረኩ ላይ እንደተናገሩት÷ በክልሉ ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ቢገኙም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ መዘናጋት ይስተዋላል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ 8 በመቶ መሆኑንና የሞት ምጣኔም 4 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የወረዳ አመራሮች ህብረተሰቡን በማንቃት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

ዓመታዊ መድረኩም በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶችን ለማረምና አበረታች ተግባራትን አጠናክሮ ከመቀጠል አንፃር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ቱፋ በበኩላቸው÷ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከሚጠበቀው በላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ ይገኛል፡፡

ለዚህም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በመጀመሪያ ሳምንት 1 ነጥብ 1 የነበረው የቫይረሱ ስርጭት በአራተኛው ሳምንት ወደ 10 ነጥብ 1 መድረሱን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላቀ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.