Fana: At a Speed of Life!

የህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ ሰራዊቱ ህውሓት ላይ ተከታታይ ድል እንዲቀዳጅ አስችሏል-ብ/ር ጀ/ል አዳምነህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) “የህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ ሰራዊቱ በአሸባሪው ህውሃት ላይ ተከታታይ ድል እንዲቀዳጅ አቅም እየሆነው ነው” ሲሉ የአማራ ክልል የሰላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ብርጋዴር ጀኔራል አዳምነህ መንግስቴ አስታወቁ።
 
ከምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደርና በስሩ ካሉ 21 ወረዳዎች ለህልውና ዘመቻው የተበረከተ የእርድ እንስሳትና የምግብ እህል ድጋፍ ርክክብ ተካሄዷል።
 
የቢሮው የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪና የጋይንት ግንባር የድጋፍ አስተባባሪ ብርጋዴል ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ትህነግ ሀገር የማፍረስ አላማውን ለማሳካት በአማራ ክልል ላይ ወረራ ፈጽሟል።
 
“አሸባሪው ቡድን በሰሜን ጎንደር፣ በዋግ ኽምራና በሰሜን ወሎ ዞኖች ላይ ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን በመግደል፣ ሃበትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም የአሸባሪነት ድርጊቱን በገሃድ አረጋግጧል” ብለዋል።
 
በተለይም በሰሜን ወሎ የጀመረውን ወረራ ወደ ደቡብ ጎንደር በማስፋት የባህር ዳርና የጎንደር ከተሞችን በማውደም ህዝቡ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ለማድረግ አልሞ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።
 
“ይሁን እንጂ የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም የሌሎች ክልሎች የጸጥታ አካላት ደብረ ታቦር አቅራቢያ የደረሰውን ወራሪ ሃይል በመመከት የማጥቃት አቅሙ እንዲሟጠጥ አድርገዋል” ብለዋል።
 
አሁን ላይ ሰራዊቱ ከመከላከል አልፎ ወደ ማጥቃት በመሸጋገር ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ደቡብ ጎንደርን ሙሉ በሙሉ ነጻ በማድረግ ደብረ ዘቢጥ ላይ በመቀጥቀጡ ጠላት እያፈገፈገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
 
የሀገሪቱ ህዝብ ለሰራዊቱ እያደረገ ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ለተገኘው አኩሪ ድል ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው የምዕራብ ጎጃም ህዝብና አስተዳደር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
 
“ድጋፉ ለሰራዊቱ የሞራልና የጀግንነት ወኔ እንዲሁም ስንቅ በመሆን ባጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረሻው ድል ያበቃናል ” ብለዋል።
 
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስሜነህ አያሌው በበኩላቸው÷“አሸባሪው ህወሓት ገና ሲፈጠር የአማራን ህዝብ ጠላት ብሎ በመፈረጅ የሀገር አንድነት ተሸርሽሮ እንዲጠፋ አልሞ ሰርቷል”ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.