Fana: At a Speed of Life!

በትዊተር የሚደረጉ ዘመቻዎች ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን የማህበረሰብ አንቂዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ)  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳት በትዊተር የሚደረጉ ዘመቻዎች የሚታዩ ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን የማህበረሰብ አንቂዎች ተናግረዋል፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የማህበረሰብ አንቂዎች እንደገለጹት÷ዘመቻዎቹ የሀገርን ስም ጥላሸት ለመቀባት ከውስጥም ከውጭም የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት እና ሀገራት የሚያራምዷቸውን የተሳሳቱ አቋሞች ለማስተካከል የሚስሉ መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡

ኑሮውን በስዊዘርላንድ ያደረገው ናትናኤል መኮንን ከዚህ ቀደም በፌስ ቡክ ይደረጉ የነበሩት እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በትዊተር እየተደረጉ ያሉ ዘመቻዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የህግ መምህሩ  እና የማህበረሰብ አንቂው ሙክታር ወይም ሙክታሮቪች ኡስማን በበኩሉ ÷ዘመቻዎቹ በተመድ የተዛባ አካሄድ ላይ የሚመለከታቸው አካላት መልስ እንዲሰጡበት እስከማድረግ ተጽዕኖ ነበራቸው ብሏል።

በቅርቡ በጋሳይ ግንባር እጁን የሰጠው የህወሓቱ ሌተናል ኮሎኔል ገብረህይወት እጅ ላይ የተገኘው ለህጻናትና እናቶች ብቻ መቅረብ የነበረበት ሃይል ሰጪ ምግብ  እና የኢትዮ ቱርክ የቅርብ ጊዜ ውይይትን በተመለከቱ ጉዳዮችና በሌሎች ሲራመዱ በነበሩ የሃሰት ትርክቶች ላይ የተደረጉ ዘመቻዎች ውጤት ነበራቸው ነው ያለው፡፡

ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ እውነትን የመከተሏንና የዜጎቿን ብዛት በሚመጥን ደረጃ አሁንም ወደ ተግባር አልገባንምና ሁሉም ከዚህ አንጻር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማገዝ እንዳለበት የማህበረሰብ አንቂዎቹ ተናግረዋል።

መንግስት በበኩሉ የዲጂታል ክንፍ በማቋቋም በዜጎች ነጻ ፍላጎት ብቻ እየተመራ ያለውን አንቅስቃሴ ማጠናከር እንዳለበት እና መረጃዎችን በሚገባ ለዘርፉ ተዋናዮች በማድረስ መልስ ከመስጠት ብቻ ወጥቶ አጀንዳ በመቅረጽ  ወደ ማጥቃት ደረጃ ሽግግር ማድረግ በቀጣይነት ይጠበቅበታል ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ÷ ባጠረ ጊዜ እንድታሸንፍ እንዲሁም ስታሸንፍ እውነቱን መላው ዓለም ተቀብሎ እንድታሸንፍ አሁንም ጥረቱ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

 

 

በአፈወርቅ አለሙ

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.