Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት -የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደር አለምፀሃይ መሰረት ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄጄ ኦዶንጎ ጋር በሁለትዮሽ፣ አካባቢያዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።
በወቅቱም የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄጄ ኦዶንጎ፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት መሆኗን አንስተው፥በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ጉዳዮች ሁሉም አፍሪካውያን በትኩረት የሚመለከቱት ጉዳይ ነው ብለዋል።
አምባሳደሯ ህወሓት በሃገርና በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የሽብር ተግባር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለሚታይ ወገንተኝነትና ያልተገባ ጫናን በተመለከተ ለሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተለይም መንግስት ለትግራይ ህዝብ ደህንነት በማሰብ የወሰነውን የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት በመናቅ የሽብር ቡድኑ ህጻናት ልጆችን በጦርነት እየማገደ፣ አጎራባች ክልሎችን በማጥቃት ንፁኃን ዜጎችን በመግደልና በመዝረፍ የሽብር ድርጊቱን እንደቀጠለበት ጠቅሰዋል።
ከዚህም አልፎ ኢትየጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ህብረት በመፍጠር አካባቢውን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ እየሞከረ እንደሆነ ይህም ለአካባቢው ሀገራትም ስጋትና አደገኛ ስለሆነ በጋራ ሊወገዝ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ሱዳንና ግብፅ ጉዳዩን በተደጋጋሚ ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እየወሰዱት እንደሚገኙ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡ የመልማት ጉዳይ በመሆኑ በፀጥታው ምክር ቤት መታየት ተገቢ አለመሆኑን መግለጿን አንስተዋል።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ስለ ህዳሴ ግድቡ ትክክል ያልሆነ መረጃዎችን በማሰራጨትና በኢትዮጵያ ላይ ግፊት በማድረግ የህዳሴ ግድቡን መጠናቀቅ ለማስተጓጎል እየሰሩ ነው ብለዋል።
የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ሉአላዊት ሃገር መሆኗን በመጥቀስ፥ የትግራይ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ መሆኑንና የሚደረጉ አላስፈላጊ ጫናዎችና ጣልቃ ገብነቶች ተቀባይነት እንደሌላቸውም አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም በአፍሪካዊ ወንድማማችነት መደጋገፍ እንጂ ከመርህ ውጪ የሆነ ጣልቃ-ገብነት ተገቢ አለመሆኑን አስምረውበታል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ የአባይን ውሃ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በብቸኝነት ለመጠቀም የሚደረግ ማንኛውንም ጥረት ኡጋንዳ በፍፁም እንደማትቀበል ጠቅሰዋል።
የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርም ሆነ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚኖር ማንኛውም ቅሬታም በዚሁ በአፍሪካ ህብረት ማእቀፍ ብቻ መመለስና መታየት እንዳለበት በአፅንኦት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገራት ያለው ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ማደግ እንዳለበት ገልጸው፥ በተለይም ረዥምና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በአካባቢያዊና ዓለም በባለብዙ መድረክ ጉዳዮች የሚያራምዱት ተመሳሳይ አቋም ለግንኙነታቸው ዋና መሰረት ነው ብለዋል።
ኡጋንዳ በእነዚህ መድረኮች በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ እምነት እንዳላትና በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.