Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ለሀገራዊ የህልውና ዘመቻ  እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ተባለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ከዞን እና ከልዩ ወረዳ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።

በዚህም ውይይት በክልሉ በወቅታዊ የልማት የመልካም አስተዳደር እና ሀገራዊ የህልውና ዘመቻ ስራው ያለበትን ደረጃ በመገምገም በቀጣይ በሚተገበሩ ስራዎች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በክልሉ  ለሀገራዊ የህልውና ዘመቻ ስኬታማነት አሁን ያለው የህዝብ ንቅናቄ የሰው ሀይል የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አበረታች መሆኑን አብራርተዋል።

እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ በድል እስኪጠናቀቅ የክልሉ ህዝብ እና መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት ።

በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በተለይ የመኸር ስራው ቀድሞ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የእርሻ ዝግጅትና የሰብል እንክብካቤ እንዲሁም የበልግ አዝመራ በደረሰባቸው አካባቢዎች ደግሞ የምርት ብክነት እንዳይከሰት በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርት አሰባሰብ ስራ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በዝናብ እጥረት ምክንያት የበልግ አዝመራ በዘገየባቸው አካባቢዎች የመኸር እርሻ ዝግጅት በማካሄድ የምርጥ ዘር ግብአት ፣የቴክኖሎጂ አቅርቦት እና ተዛማጅ  ስራዎችን በማከናወን  በበልግ ወቅት ይባክን የነበረውን ምርት ለማካካስ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይታቸው ጠቁመዋል።

ለዘርፉ የግብርና ስራ ስኬታማነት የአመራሩ እና የባለሙያው ድጋፍ ከፍተኛ ሊሆን ይገባልማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.