Fana: At a Speed of Life!

የአሸባሪው ወረራ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት እንዲነሱ አድርጓል – አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት የሽብር ቡድን ወረራና ጥቃት ኢትዮጵያውያንን ለህልውና ዘመቻው ከዳር እስከ ዳር በጋራ እንዲነሱ ያደረገ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

የአማራና የቅማንት ህዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ ወንድማማችነት በጽንፈኞችና በጸረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች አይበረዝም በሚል መሪ ቃል ዛሬ በጎንደር ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ የተረዱ ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በስፋት በመንቀሳቀስና በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል በጋራ መክተው በመመለስ አኩሪ ጀግንነት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጎንደርና አካባቢው ህዝብ በግንባር ለተሰለፈው ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ደጀንነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ዘምቶ በመፋለም ያሳየው ጀግንነት ታላቅ ክብር የሚያሰጠው ነው ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ወገን ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ይገኛል ያሉት አፈ ጉባኤው÷ ቀሪ ስራዎችን በማከናወን የሽብር ቡድኑ የወረራቸውን አካባቢዎች ነጻ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የቅማንትና አማራ ህዝቦችን የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች በመናድ የሽብር ቡድኑ ከፋፋይ ተልእኮ አስፈጻሚ በመሆን የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ህዝቡ በጋራ ሊታገላቸው እንደሚገባም አፈ ጉባኤው አደም ፋራህ አሳስበዋል።

መንግስት ከሀገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን የጀመረውን የሰላም ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ የሁለቱ ህዝቦች ዘመናትን የዘለቀው የአብሮነት እሴቶች በሴረኞችና ከፋፋዮች የሽብር ተግባር ሊሸረሸር አይገባውም ብለዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን ተላላኪ በመሆን የእነሱን ተልእኮ ለማስፈጸም በሚደረግላቸው የገንዝብ ድጋፍ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት የሚጥሩ ሃይሎችን ህዝቡ አጥብቆ ሊታገላቸው እንደሚገባ መናገራቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቅማንትና አማራ ስም የሚነግዱ ቡድኖችን ህዝቡ አጋልጦ ለህግ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ከቅማንት ኮሚቴ ጋር የተጀመረው በጎ ውይይትና ድርድር በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ ከጎንደር ከተማና አካባቢው የተውጣጡ የቅማንትና አማራ ተወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከፌደራል ክልል ዞንና ወረዳ የመጡ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.