Fana: At a Speed of Life!

ሕገ-ወጥ መድኃኒት ሲሸጡ የተገኙ አምስት መድሃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በሆስፒታሎች አካባቢ በሚገኙ መድሃኒት ቤቶች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሕገ-ወጥ መድኃኒት ሲሸጡ በተገኙት አምስት ፋርማሲዎች ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

መድሃኒት ቤቶቹ እንደ ጥፋታቸው ደረጃ ከሶስት ወር እስከ አንድ ዓመት እንዲታሸጉ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ አጫሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ሣምንት በጳውሎስ፣ በራስ ደስታና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች አካባቢዎቸ በሚገኙ ዘጠኝ መድሃኒት ቤቶች ላይ በተደረገ ፍተሻ አምስቱ ሕገወጥ መድኃኒት ሲሸጡ ተገኝተዋል።

መድሃኒት ቤቶቹ ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ እርምጃው የተወሰደው ከኅብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሆኑን ጠቁመዋል።

መድሃኒት ቤቶቹ በአገር ውስጥ ያልተመዘገቡ፣ ከባለስልጣኑ ፍቃድ ያላገኙ፣ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ፣ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ያልተሰጣቸው፣ ጥራታቸውን ያልጠበቁ፣ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድሃኒቶችን ሲሸጡ ተገኝተዋል ብለዋል።

ከእነዚህም መካከል በመንግስት ተቋማት ብቻ ለካንሰር ህሙማን የሚሰጡ መድኃኒቶችና የኬሞቴራፒ መድኃኒቶች በሕገወጥ መንገድ ከሚሸጡት መካከል ጠቅሰዋል።

ያለ ሐኪም ትዕዛዝና ያለ ደረሰኝ የሚሸጡና ስርዓት ያልተከተሉ መድሃኒት ቤቶች ላይም እርምጃ የመውሰዱ ተግባር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኅብረተሰቡ መድሃኒቶችንና ምግብ ነክ ምርቶችን ሲገዛ የመጠቀሚያ ጊዜው አለማለፉን ማረጋገጥ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሕገወጥ ነጋዴዎች ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው ስለሚሸጡ ኅብረተሰቡ በተለይ በርካሽ ዋጋ የሚሸጡ ምርቶችን ሲገዛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.