Fana: At a Speed of Life!

ኬንያ ለኢትዮጵያ ሰላም እና ብልፅግና ድጋፏን ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) ኬንያ ለኢትዮጵያ ሰላም እና ብልፅግና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይሸል ኦማሞ አስታወቁ፡፡

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በሱዳን እና የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ እና በአሸባሪው ህወሓት ትንኮሳና እና ጥቃት በሰሜናዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች ስለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ዙሪያ አቶደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል፡፡

ኬንያ በመንግስታቱ የፀጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆሟ ለሃገሪቱ መንግስትና ህዝብ ታላቅ ምስጋና እና አክብሮት እንዳላቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይሸል ኦማሞ በበኩላቸው ሃገራቸው በሁሉም መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል እና ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ሉዓላዊነት፣ ግዛታዊ አንድነትና ብልጽግና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ኬንያ እና ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የተሳሰረ እና ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው የተናገሩት አምባሳደር ራይሸል÷ የሁለቱን ሃገራት ጥምረት በመሰረተ ልማት፣ በኢኮኖሚዊ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አውስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በሁሉም የትብብር መስኮች የበለጠ ተቀራርባ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዳላት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.