Fana: At a Speed of Life!

የ5 ዓመት የስርአተ ጾታና አካታችነት ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤና ሚኒስቴር የ5 ዓመት የስርአተ ጾታና አካታችነት ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ እና ሌሎች የስራ መመሪያዎችን ይፋ አደረገ፡፡

በስትራቴጂክ እቅዱ ስርአተ ጾታን ማካተት፣ ሴቶችን ማብቃትና ጾታዊ ጥቃትን መከላከልና አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ተካተዋል ተብሏል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የሴቶች፣ ህጻናትና የወጣቶችን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች መሰረት ያደረጉ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን የማሻሻል ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት ያጋጠማቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና ተጠቃሚነት የማሳደግና የማረጋገጥ ተግባራት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል።

በጤናው ዘርፍ የስርአተ ጾታና አካታችነት ትግበራን የሚያሳልጡ ስትራቴጂዎችና ሌሎች መመሪያዎችን በመንደፍ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽነት ማስፋት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል።

በዚህም የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ እንዲሁም የስራ ቦታ ትንኮሳን ለማስቆምና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና ሴክተር የስርአተ ጾታ ማካተቻ እና ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት በመስጠት በተለይ የምልክት ቋንቋን በጤና አገልግሎቶች ለማስፋፋት የሚያስችል የስልጠና እና የአተገባበር መመሪያም የተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.