Fana: At a Speed of Life!

በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ የአማራ ክልል ሴቶች ለልዩ ሃይሉ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ሴት ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለሀገር ዋጋ እየከፈሉ ላሉ ጀግኖች ደጀንነታቸውን ለማሳየት “የዘመኑ ጣይቱዎች እንሁን” በሚል መሪ ቃል 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በማሰባሰብ የገዟቸውን የተለያዩ ቁሳቁስ ለክልሉ ልዩ ኃይል ድጋፍ አድርገዋል።

4 ሺህ 200 የሚሊተሪ ቦርሳ፣ የስንቅ መያዣ እና የንፅህና መጠበቂያን ጨምሮ የገዟቸውን የተለያዩ ቁሳቁስ ለዘመቻው የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴና ለልዩ ኃይል አመራሮች በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።

በሰላም መኖር፣ መስራትና መበልፀግ የሚቻለው በሀገር ነው ያሉት የሃሳቡ አፍላቂ ባለሀብት ወይዘሮ ትልቅሰው ገዳሙ፥ “ከገንዘብ ባሻገር በጉልበትና በግንባር እስከመሰለፍ ከጎናችሁ ነን” ሲሉ ለሠራዊቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ድሉ ፍትህ ከተነፈገው ህዝብና ሠራዊት ጋር ስለመሆኑም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ቀያቸው ለወደመባቸው ቤት ከመስራት፣ ሰው የሞተባቸውን ከማፅናናት እና ሠራዊቱን ከመደገፍ ባሻገር ለዘማች ቤተሠብ የዓመት በዓል መዋያ ለማበርከት ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በኢትዮጵያ ታሪክ በተደጋጋሚ እንደታየው እንዲህ ያለው ወቅት የሀገር ዋልታ የሆኑ ጀግኖች የሚፈጠሩበት ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ዘግናኝ ወንጀሎችን እየፈፀመ ስለመሆኑ በመግለፅ የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት የተጀመረው የጋራ ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

የአማራ ልዩ ሀይል የሎጂስቲክስ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ እሸቴ በበኩላቸው ለሠራዊቱ የተደረገው ድጋፍ ወቅታዊና የሴቶችን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.