Fana: At a Speed of Life!

በሻሸመኔ ዘመናዊ የመብራት ምሰሶዎች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም- ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሻሸመኔ ከተማ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የተገነቡት ዘመናዊ የመብራት ምሰሶዎች አስፈላጊውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አቀረቡ።

ነዋሪዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ÷ምሰሶዎቹ የከተማዋን ውበት ከማድመቅ ውጪ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ።

የመብራት አገልገሎት ቢሰጡ የከተማዋን ፀጥታ ለማረጋገጥ ላቅ ያለ ድርሻ ይኖራቸው ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ ክፍተኛ የህዝብ ሀብት ወጪ ተደርጎባቸዉ የተተከሉት ምሰሶዎቹ ያለ አገልግሎት ዓመታትን እየተሻገሩ መባከናቸውን ጠቅሰዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በበኩሉ÷ ምሰሶዎቹ መጀመሪያ ሲተከሉ የቴክኒክ ችግር የነበረባቸው መሆኑ አገልግሎት ላለመስጠታቸው ምክንያት ነው ብሏል።

የማዘጋጃ ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ገመዳ የመብራት ሽቦዎች በሌቦች በመሰረቃቸው ምክንያት በዋናነት አገልግሎት እንዳይሰጡ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

ምሰሶዎቹ የመብራት አገልግሎት እንዲሰጡ በ2013 ዓ.ም በ6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎ መጠገናቸውን ተናግረዋው በተደረገላቸው ጥገና ምሰሶዎቹ በተተከሉበት መስመሮች ላይ አሁን የመብራት አገልግሎት መስጠት እንደ ጀመሩም ነው የገለጹት።

የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ይህን ይበሉ እንጂ በምሰሶዎቹ ችግርና መፍትሔ ላይ በተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሲሰራ የቆየው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጋዜጠኞች ቡድን ሌሊት አሰማርቶ ባደረገው ምልከታ ከማዘጋጃ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ቃል በተቃራኒ ከ8 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ምሰሶዎች ውስጥ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ በቁጥር አናሳ የሆኑ ብቻ እንደሚበሩ አረጋግጧል።

በቢቂላ ቱፋ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.