Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ ተቋማት በህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ ተቋማት አሸባሪው የትህነግ ቡድን ግፍ የፈጸመባቸውን ዜጎች በመደገፍ አጋርነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር አሳሰቡ፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ኀላፊ ማርሲ ቪጎዳ ጋር ተወያይተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል ወረራ ፈጽሞ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋቸዋል።
ንጹሐን ዜጎችን በአስቃቂ ሁኔታ እየገደለና እያሳደደ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ ከ550 ሺህ በላይ ዜጎቻችን እንዲፈናቀሉ አድርጓል ብለዋል።
የሽብርተኛውን ትህነግ ቡድን ሀገር የማፍረስ ተግባር እና በዜጎቻችን ላይ ያደረሰውን ጥቃት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ እያሳደዳቸውና እያፈናቀላቸው ላሉ ዜጎቻችን ሰብዓዊ ድጋፍ ከማቅረብ ጀምሮ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው ነው ያሉት።
እየተሳደዱና እየተጠቁ ላሉት ዜጎቻችን ድምጽ የሚሆኗቸውና ከጎናቸው የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ማዬት እንሻለን፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮም የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ጉዳይ ተረድቶ ድጋፍ እንዲያደርግ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድ ዶክተር ርፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው÷ አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ግልጽ ወረራና ጥቃት ፈጽሞ ንጹሐን ዜጎች የጤናና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት እንዳያገኙ እየዘረፈና እያወደመ ስለመሆኑ ለሃላፊው አስረድተዋቸዋል።
የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት እንዲያጣ ማንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲደርሱበት አሸባሪው ትህነግ መሪ ተዋናይ ሆኖ እየሠራ ነው፤ በመላ ሀገሪቱ የሚኖር ሕዝባችንን እያስጨፈጨፈ ነው፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህንን በመገንዘብ ከተበደሉ ዜጎች ጎን ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ኀላፊ ማርሲ ቪጎዳ ተቋማቸው ለአማራ ክልል ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 148 ሚሊዮን ብር መመደባቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቋማቸው በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ የሚያደርግ በመሆኑ በቀጣይም ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመርዳት ዝግጁ ነን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.