Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ አቅርቦት ለዜጎች በአግባቡ እንዲደርስ በህወሓት ላይ ተገቢውን ጫና እንዲያሳድር ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነባራዊ ሁኔታውን በተገቢው በመገንዘብ በአሸባሪ ቡድኑ ምክንያት እየተስተጓጎለ ያለውን የእርዳታ ስርጭት ለዜጎች በአግባቡ እንዲደርስ ተገቢውን ጫና እንዲያሳረፍ ተጠየቀ፡፡
 
የሰላም ሚኒስቴር በትግራይ ክልል እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች እስካሁን እየተካሄደ ያለውን የእርዳታ አቅርቦት ስርጭት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል ሰብዓዊ ተኩስ አቁም ለማድረግ ከመወሰኑ በፊት በክልሉ ለሚገኙ እርዳታ ላስፈለጋቸው 4.9 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እርዳታ ስርጭት በሶስት ዙር ማከናወኑ ይታወሳል።
 
የተናጠል ተኩስ አቁም ለማድረግ በወሰነበት ወቅትም ከመንግስትም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችም ለሁለት ወራት ገደማ የሚሆን የእርዳታ እና የመድሃኒት አቅርቦት እንዲሁም ከግማሽ ሚሊየን ኩንታል በላይ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በቦታው አኑሮ መውጣቱም ይታወቃል።
 
ሂደቱን ተከትሎ ቀደም ሲል በመንግስት አስተባባሪነት በክልሉ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ስድስት ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች አማካኝነት የእርዳታ ስርጭቱ ቀጥሏል።የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴው በብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ የሚኒስትሮች ኮሚቴ የሚመራ ሲሆን የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ፣
 
በእስከ አሁኑ ሂደት ትናንትና እና ዛሬ የተንቀሳቀሱትን 152 መኪኖች ጨምሮ በድምሩ 500 ገደማ መኪኖች የግብርና ግብዓቶችን (ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ)፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዘዋል።
 
ይሁን እንጂ በጥፋት ቡድኑ በተደጋጋሚ በአፋር እና አማራ ክልል በተካሄደው ወረራ እና በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ባለው ጥቃት ምክንያት እንዲሁም የእርዳታ መተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ በሚፈጽመው ጥቃት እርዳታ የማድረስ ሂደቱን ውስብስብ አድርጎታል።
ቀደም ሲል ከመነሻው እስከ መዳረሻው የነበሩ ሰባት የፍተሻ ጣቢያዎችን ወደ ሁለት የፍተሻ ጣቢያ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።
 
ይህ ሂደት የሚከናወነው ከማዕከላዊ መጋዘን ወይም ከወደብ ጀምሮ ተገቢውን የፍተሻ ሂደት አልፈው አግባብነት ባላቸው አካላት ታሽጎ በህግ አስከባሪ አካላት ታጅቦ በአፋር ክልል የሚገኙ ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ በፍተሻ ማሽን እና/ወይም በሰው ኃይል የመጨረሻ ፍተሻ በማከናወን ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ ይደረጋል።
 
የገንዘብ መጠንን በተመለከተ ቀደም ሲል የነበረውን ጣሪያ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍን ለማሳለጥ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ ድርጅቶች ባላቸው የስራ ስፋት እና የሰው ኃይል መጠን ተመስርቶ እንዲሻሻል ተደርጓል። እስከ አሁንም በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ 28 የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች አለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል።
 
ወደ ክልሉ ለሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት ለሚጓዙ ሰራተኞች የ48 ሰዓት የኢሜይል ቅድመ ማሳወቂያ ስርዓት እንደነበረው እንዲቀጥል ተደርጓል። ይሁን እንጂ በአሸባሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ በአፋር እና አማራ ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት 4.5 ሚሊየን ዜጎች ለጉዳት የተዳረጉ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
 
ሆኖም ግን መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየቀረበ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አሁንም በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ ሆኖ ይገኛል።
 
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው የገቡ ከባድ ተሽከርካሪዎች በተቀመጠው የአሰራር ስርዓት መሰረት ተመልሰው መውጣት ሲገባቸው አለመመለሳቸውን በተደጋጋሚ ብናሳስብም ተገቢው ምላሽ አለመገኘቱ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢና ጥርጣሬያችንን እጅግ የሰፋ አድርጎታል።
 
በተጨባጭም ከአላማቸው ውጭ ተሰማርተው ላለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል አልተገኘም። ይህ ሁኔታ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ነባራዊ ሁኔታውን በተገቢው በመገንዘብ በአሸባሪው ቡድኑ ምክንያት እየተስተጓጎለ ያለውን የእርዳታ ስርጭት ለዜጎች በአግባቡ እንዲደርስ ተገቢውን ጫና ማሳረፍ እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.