Fana: At a Speed of Life!

ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገቡ ታገደ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ደረጃዎች አጀንሲ በቅርቡ በአስገዳጅነት ደረጃ እንዲወጣላቸው ከተደረጉ ምርቶች መካከል የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ `ዲቫይደር` እና ሃይል ቆጣቢ አምፖሎች የኢትዮጵያን ደረጃ ባለማሟላታቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ታገዱ፡፡

ምርቶቹ በአስገዳጅነት ደረጃ ከወጣላቸው በኋላ አምራቾቹ በወጣላቸው ደረጃ መሰረት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ለአራት ወራት የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

በዚህም መሰረት ኤጀንሲው ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቁጥጥር የገባ ሲሆን፥ ቁጥጥር በሚደረግበት ጊዜ የተጠቀሱት ምርቶች በላቦራቶሪ ፍተሻ በሚደረግበት ጊዜ የኢትዮጵያን ደረጃ ሳያሟሉ ቀርተዋል ነው የተባለው፡፡

በፍተሻ ወቅት 21 የማከፋፈያ አይነቶች ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ፣ ሀይል የሌላቸውና የተላላጡ ሆነው መገኘታቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በዚህ ምክንያት ከ10 በላይ አስመጪዎች ምርቶቻቸው ከደረጃ በታች ሆነው በመገኘታቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳያስገቡ መከልከላቸውን የገቢና ወጪ ዕቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሳምሶን ገልፀዋል፡፡

ማንኛውም አስመጪ እንደዚህ አይነት ችግር መኖሩን አውቆ ምርቶቹን ከማስመጣቱ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

መንግስት በእንደዚህ አይነት ጥራት የጎደላቸው ምርቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ስለሚያደርግ አስመጪዎች ራሳቸውንና ሀገራቸውን ከኪሳራ እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.