Fana: At a Speed of Life!

ጁንታው በሶስት አቅጣጫ ያሰለፈው ሃይል ሙሉ በሙሉ ተደመስሷል – ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ጁንታው በሶስት አቅጣጫ ያሰለፈው ሃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ገልጸዋል፡፡

ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግስት በተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርግም አሸባሪው ቡድን አሻፈረኝ በማለት ያለ የሌለ ኃይሉን በማሰለፍ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ አድርጓል፡፡

ሆኖም ብርጋዴር ጄነራል ምግበ በሚባል ከሃዲ ግለሰብ የሚመራው አርሚ አንድ የተሰኘው ኃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ጁንታው በ10ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን ያሰለፈ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ ውድመት እየደረሰበት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም ከ5ሺህ 600 በላይ ታጣቂዎች ሲደመሰሱ÷ ከ2ሺህ 300 በላይ ታጣቂዎች ሲቆስሉ÷ 2ሺህ ሰዎች ተማርከዋል፡፡

የተቀሩት ስልጠና የሌላቸው እና በፍላጎትም እየተዋጉ ባለመሆኑ እግሬ አውጭኝ በማለት ፈርጥጠዋል፡፡

በውጊያ ወቅት የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸውን በመግደል እንደሚሸሹ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ገልጸዋል፡፡

መተማን ወደ ቀኝ በመተው በሽንፋ በኩል ወደ ጎንደር በመግባት በቅማንት ስም የተደራጀ ቅጥረኛ ቡድን ጋር በመተባበር ለሽብር ተግባር ተልዕኮ የነበረው ኃይልም 90 አባላቱ ሲገደሉ ቀሪዎቹ ወደ መጡበት ሸሽተዋል፡፡

በውጪ ከሚያደራጃቸው ከሃዲው ሜጀር ጄኔራል ፍሰሃ ተልዕኮ የሚቀበለው ኃይል ከዚህ በፊትም ሁለት ጊዜ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኩል በመግባት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራን ለማስተጓጐል ጥረት ቢያደርግም ያሰበውን ሳያሳካ ተመቶ ተመልሷል፡፡

በአጠቃላይ በጦርነቱ ከ10 ሺህ በላይ የአሸባሪው ኃይል ተደምስሷል፡፡

ጁንታው በጦርነቱ ያሰለፋቸው ህፃናት ከሁለት ቀን ያልበለጠ ስልጠና የወሰዱ ከመሆናቸውም ባሻገር እንዳሸሹ ከኋላ ገዳይ ኃይል እንደሚመድቡም ተናግረዋል፡፡

ሌተናል ጄነራል ባጫ ጦርነቱ አሁንም የቀጠለ መሆኑን በማውሳት÷ በተገኘው ድልም ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.