Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል የማረሚያ ቤት ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ የደንብ ልብስ ፣ ማእረግና አርማ አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል የማረሚያ ቤት ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ መልክ የቀየረውን የደንብ ልብስ ፤ የማእረግና አርማ ምልክት በዛሬው እለት በጅግጅጋ ከተማ አስመርቋል።
በዚህ ስነ ስርአት ላይ የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ፣የፌደራል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ ፤ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ኮሚሽነር አቶ በሽር አህመድ እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የኮሚሽኑ የፖሊስ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።
በስነስርአቱ ላይ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ፤ ከፌደራልና ከክልሉ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጋር በመሆን የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን አዲሱን የደንብ ልብስ ፣ ማእረግና አርማ በይፋ መርቀዋል።
አመራሮቹ ማረሚያ ቤቶቱ ከተቀቋመ ጀምሮ እስካሁን የደረሰበትን ሂደቶችንና በማረሚያ ቤት ታራሚዎች የተሰሩ ስራዎችን ለማሳየት የተዘጋጀውን አውደ ርዕይንም ጎብኝተዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዳመነ ዳሮታ፥ ባለፉት ሶስት አመታት በሀገሪቱ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶቻቸው ተጠብቆ የማረም ማነፅ ስራቸውን በማከናወን በኩል ሰፊ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
የሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤት የደንብ ልብስ ፣ ማእረግና አርማ ተቀይሮ መብቃት በዘርፉ እየተካሄዱ ከሚገኙ የለውጥ ስራዎች መካከል አንዱ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ፥ የክልሉ መንግስት በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የተፈጠሩ ለውጦችን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው፥ ባለፉት 27 አመታት በአሸባሪው ህወሃት አገዛዝ ወቅት በሀገሪቱ ሆነ በክልሉ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የተሳሳቱ ሰዎች የሚታረሙበት ሳይሆን ንፁሀን ዜጎች የሚሰቃዩበት የሰቆቃ ማእከል እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ከለውጡ በኋላ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሳደግ በርካታ የለውጥ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
ርእሰ መስተዳደሩ አያይዘውም በአዲስ መንፈስና አስተሳሰብ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ባለፉት ሶስት አመታት የተመዘቡ ውጤቶች አጠናክረን ለማስቀጠል መረባረብ ይገባል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በሽር አህመድ፥ በክልሉ ከለውጡ በፊት በነበሩ አመታት የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ዜጎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት በክልሉ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች አያያዝን ከማሻሻል ባለፈ ታራሚዎችን ትምህርትና ሞያ በማሰልጠን አምራች የህብረተሰብ ክፍል እንዲሆኑ ሰፊ ስራ መሰራቱን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
ኮሚሽነሩ የማረሚያ ቤት ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ ፤ ማእረግና አርማ በአዲስ መቀየር ያስፈለገበት ከዚህ ቀደም በክልሉ ማረሚያ ቤት የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ከህዝቡ ህሊና ለማጥፋትና የማረሚያ ቤት ፖሊስ ወቅቱን ያገናዘበ አልባሳትና አርማ እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
በስነስርአቱ ላይ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመነ ዳሮታ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በክልሉ ማረሚያ ቤት ለውጥ እንዲመጣ ላከናወኑት ሰፊ ስራዎች ልዩ ሽልማት ያበረከቱላቸው ሲሆን በመድረኩ ላይ ለክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር በሽር አህመድ የማበረታቻ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ከክልሉ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.