Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ቡድኖቹ ለግጭት የሚመርጧቸውን አካባቢዎች በልማት በማስተሳሰር እኩይ ዓላማቸውን ማክሸፍ ይገባል- ዶ/ር አህመዲን መሀመድ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የሽብር ቡድኖቹ ለግጭት የሚመርጧቸውን አካባቢዎች በልማት በማስተሳሰር እኩይ ዓላማቸውን ማክሸፍ ይገባል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ  ዶክተር አህመዲን መሀመድ ገለጹ።

በአፋር ክልል ዞን አንድ አደኤላ ወረዳና እና በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማስወገድ በሚቻልበት ዙሪያ አምራሮቹ ከህዝቡ ጋር ተወያይተው የደረሰቡትን ደረጃ በሸዋሮቢት ከተማ በጋራ ገምግመዋል።

የወረዳዎቹ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሁለቱ ህዝቦች መካከል የግለሰቦችን ግጭት ወደ ህዝብ በማሳደግና አሉባልታ በመንዛት የአካባቢውን ሰላም መበጥበጥ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ፥ የሽብር ቡድኖቹ አካባቢውን ለግጭት የሚመርጡት በመሆኑ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከርና በልማት በማስተሳሰር እኩይ ዓላማቸውን ማክሸፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለሚኖረው ዘላቂ ሰላም የሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ጥፋተኛን ለይቶ እርምጃ መውሰድና አሉባልታን ማስወገድ ላይ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የአጣየና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ተወካይ አስተባባሪ ኮሎኔል ተከተል ልኬ፥ ሁለቱ ህዝቦች በእጃቸው ያለውን ሰላም ለማንም አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ ፥ሁለቱ ህዝቦች በመካከላቸው ያለውን ጠላት ነጥለው በመምታት ወንድማማችነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የእነዚህን አካላት እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ እንደሚሰሩ የተናገሩት የሀይማኖት አባቶቹና የሃገር ሽማግሌዎቹ ወንጀል የሚፈፀሙ አካላትን ለህግ በማቅረብ ረገድ በመንግስት የፀጥታ አካላት በኩል ክፍተት እንዳለም አንስተዋል።

ሁለቱ ህዝቦች በአሉባልታ፣ በግለሰቦች ግጭት፣ በእርሻ መሬት እና በከብቶች ስርቆት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመነጋገር በመፍታት ፊታቸውን ወደ ልማት ለማዞር ቃል በመግባት ከስምምነት ላይ መደረሱን ከሰሜን ሸዋ ዞን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.