Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪው ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት የደረሰበት የጋሳይ ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ የጤና አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት የደረሰበት የጋሳይ ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ የጤና አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በደቡብ ጎንደር ዞን በፋርጣ ወረዳ የሚገኘው የጋሳይ ጤና ጣቢያ በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ደርሶበት እንደነበረ ይታወሳል።

አሸባሪ ቡድኑ ከተደመሰሰ በኋላ በአሁኑ ወቅት ጤና ጣቢያው ጥገና እየተደረገለት መሆኑን የፋርጣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰለሞን ታደሠ ተናግረዋል።

ጤና ጣቢያው መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች መስጠት የሚያስችለው መድኃኒት በማግኘቱ አሁን ላይ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ኃላፊው አስረድተዋል።

የወረዳው አስተዳደር ለጥገና የሚውል 90 ቆርቆሮ ድጋፍ ማድረጉን ኀላፊው ተናግረዋል።

የደብረ ታቦር ሪፈራል ሆስፒታልም ጤና ጣቢያው አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የመድኃኒት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የፋርጣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤትም ለድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች ለጤና ጣቢያው እያሟላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ውድመቱን የሚያጠናና ሀብት በማፈላለግ ተቋሙን የመልሶ ማቋቋም ሥራ የሚተገብር ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች በቦታው በመገኘት ጅምር እንቅስቃሴውን እንደተመለከቱና የጉዳቱን መጠን በመለየት ድጋፍ የመስጠትና ሃብት የማሰባሰብ ሥራ ለመሥራት ቃል መግባታቸውን ኃላፊው መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.