Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ሱዳን በግዛቷ የኢትዮጵያን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ እንዲደረግ አትፈቅድም-ፖል ማዮም አኬች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ደቡብ ሱዳን በግዛቷ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ በፍጹም አትፈቅድም ሲሉ የደቡብ ሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፖል ማዮም አኬች ገለጹ።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መህዲ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በተወያዩበት ወቅት ነው።
አምባሳደር ነቢል በወቅቱም የሁለቱ አገራት ህዝቦች ለዘመናት የዘለቁ ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ሪፎርሞችን አስመልክተውም ለሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አሸባሪው ህወሓት የሪፎርሙ አካል እንዲሆን በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ሀገር የማፍረስ ሴራ ላይ መጠመዱንም ገልጸውላቸዋል።
በዚህም የህወሓት አሸባሪ ቡድን የአፋር እና የአማራ ክልሎችን በመውረር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማፈናቀል ፣ ሰላማዊ ዜጎችን በመጨፍጨፍና የህዝብ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ስራ ላይ ተጠምዷል ብለዋል።
አያይዘውም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተደረገ ስላለው የሦስትዮሽ ውይይትም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሳታሳድር የዓባይን ውኃ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም አቋሟን ይዛ የምትቀጥል መሆኑንም ነው የገለጹት።
የሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖል ማዮም አኬች በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ያደረገችው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት በጠንካራ የባህልና ታሪካዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ተራማጅ መሆኑን ሲናገር የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ዘረኛ እና ተገንጣይ ቡድን መሆኑን በግልጽ አሳይቷል ብለዋል።
ፖል ማዮም አያይዘውም የትግራይ ጉዳይ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ፥ አሸባሪውን ቡድን ተጠቅመው በአፍሪካ ቀንድ ብጥብጥን ለማባባስ ሙከራ የሚያደርጉ ስውር እጆች በመኖራቸው ይህ ጉዳይ በቀጠና ደረጃ በሚደረግ ዲፕሎማሲያ ጥረት መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል።
በውይይት ስም የሚደረግ የመንግሥት ለውጥ ተቀባይነት የለውም፤ የደቡብ ሱዳን ግዛትም የኢትዮጵያን ጥቅም አደጋ ላይ ለሚጥል የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ጥቅም ላይ እንዲውል አንፈቅድም ብለዋል።
የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ተሳታፊ ባልሆኑበት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ላይ ተመስርቶ መጓዝ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፣ የዓባይ ውኃን ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ለጋራ ልማት ሊጠቀሙበት ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.