Fana: At a Speed of Life!

ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸነፊ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የመንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

የ2013 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በአዲስ አበባ  ተካሄደ ።

ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በአስር ዘርፎች ከ500 በላይ ዕጩዎች ተጠቁመው፥ ከእነዚህ መካከል 30 ሰዎች የመጨረሻ ዕጩ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

በዛሬው ዕለትም በአስር ዘርፎች ለመጨረሻ ዕጩ ከቀረቡት ሶስት ሶስት ዕጩዎች ውስጥ የመጨረሻ አሸናፊዎች ይፋ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የመንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን አሸንፈዋል።

በመምህርነት ዘርፍ ዶክተር ልዑልሰገድ አለማየሁ፤ በበጎ አድራጎት ዘርፍ አቶ አማረ አስፋው፣ በቅርስና ባህል ጥበቃ ዘርፍ ቢላል ሃበሽ የማህበረሰብ ሙዚየም ማዕከል፣ በሳይንስ ዘርፍ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ፣ የማህበራዊ ጥናት ዘርፍ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ በንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ አቶ በላይነህ ክንዴ ፣በዳያስፖራ ዘርፍ  አቶ ኤሊያስ ወንድሙ  ማሸነፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አቶ ኤሊያስ ወንድሙ ከሀገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ስለኢትዮጵያ ሲሉ ብዙ መድከማቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም የ2013 የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ሆነዋል።

ፀሀፊ ትዕዛዝ ስለ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የፈጸሙት ጀብድ ከታሪክ ማህደራቸው ተነቧል። በዲፕሎማሲው የሠሩት ታሪክ መቼም አይዘነጋም ተብሏል።

የበጎ ሰው ሽልማት በኢትዮጵያ በጎ የሰሩ እና ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ማበረታታት እና እውቅና ለመስጠት ዋና ዓላማ አድርጎ በየዓመቱ የሚካሄድ ሽልማት ነው።

 

ፎቶ ከፕሬስ ድርጅት

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.