Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 3 ዓመታት ከ227 ቢሊየን ብር በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውል ተፈጽሟል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ227 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው129 የግንባታ እና 30 የከባድ ጥገና ፕሮጀክቶች የውል ስምምነት መፈጸሙን የትራንሰፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ÷በመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም በክፍተት ከተለዩ ጉዳዮች አንዱ እምቅ አቅምና ለሀገር ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ወሳኝ ኮሪደሮች አለመከፈታቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታትም ባለፉት ሶስት ዓመታት በ”GTPII” ተይዘው የነበሩ የተለዩ ትላልቅ ኮሪደሮችን ግንባታ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በባሌ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሌሎች አካባቢዎች በማስጀመር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ትስስር ትኩረት የተሰጠውና ባለፉት ሶስት ዓመታት የእቅድ አካል የሆነው ማንዳ ቡሬ፣ ነጌሌ ቦረና ዶሎኦዶ መልካሱፍቱ፣ ነጆጃርሶ ደቡብ ሱዳን በእቅዱ ተካተው መጠግበራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የግንባታ ፕሮጀክቶች የፊዚካል ስራዎች በነባር መንገዶች ማጠናከር፣ በነባር መንገዶች ደረጃ ማሻሻል፣ የአዳዲስ መንገዶች እና የፍጥነት መንገዶች ግንባታዎች 3 ሺህ 741 ኪሎ ሜትር ተከናውነዋል፡፡
የመንገድ ከባድ ጥገና እና ወቅታዊና መደበኛ ጥገናዎችን ባለፉት ሶስት ዓመታት 30 ሺህ 865 ኪሎ ሜትር ማከናወን መቻሉንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ላለፉት ሰባት ዓመታት አገልግሎት በመስጠት ከ40 ሚሊየን በላይ የተሽከርካሪ ፍሰት በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ገቢ ማስገኘት መቻሉም ተመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.