Fana: At a Speed of Life!

ወራሪው ጁንታ የአፋር ህፃናትና ሴቶችን ቢገድልም እኛ የትግራይን ህዝብ ህይወት እያዳንን ነው – የአፋር ክልል

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልላዊ መንግስት ህወሓት በክልሉ ወረራ በመፈጸም ንፁሃን አርብቶ አደሮችን እየጨፍጨፍ ቢሆንም ለወንድም የትግራይ ህዝብ ሲባል ህይወት አድን የሰብዓዊ ድጋፍ በክልሉ በኩል እንዲተላለፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የአፋር ክልል መንግስት፣ የፀጥታ አካላት እንዲሁም የጎሳ መሪዎች ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙም በመግለጫው አመልክቷል።

አሸባሪው ህወሀት በአፋር ላይ ወረራ ከመፈጸም አልፎ በፈንቲ ረሱ ጋሊኮማ በተባለ ቦታ ላይ በንፁሃን አርብቶ አደሮች፣ ህፃናት፣ ሴቶችና ሽማግሌዎች ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጭፍጨፋ አካሂዷል፡፡

በዚህም ህወሓት ለአፋር ህዝብ ያለውን ጥላቻ፣ ንቀትና አረመኔያዊነት ቢያሳይም ከወንድም የትግራይ ህዝብ ጋር አብሮ የኖረው የአፋር ህዝብ በክልሉ በኩል ለትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከአለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ነው ብሏል።

በቅርቡ ከመቶ በላይ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ እንዲያልፉ መደረጉንም ነው የገለጸው።

መግለጫው አክሎም የአፋር መንግስትና ህዝብ ለጉዳዩ እንዲህ የተለየ ትኩረት ሰጥተው ሰብዓዊነት ተሰምቷቸው እርዳታው እንዲያልፍ ያደረጉት ለትግራይ ህዝብ ብቻ እና ብቻ ሲባል ነው ብሏል።

ጁንታው በአፋር በኩል በተለያዩ ግንባሮች የሰብዓዊ ጥሰት እና ዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈፀም ሙከራ ቢያደርግም የአፋርን ህዝብ ብርቱ ክንድ ቀምሷል ።

አሁንም ቢሆን ከዚህ ድርጊቱ የማይቆጠብ፣ ከቅዠቱ የማይወጣና ቆም ብሎ የማያስብ ከሆነ የአፋር ህዝብና መንግስት የመጨረሻ እርምጃ እንደሚወስዱ ነው ክልሉ ያስገነዘበው።

የትግራይ ህዝብም ይህን ለተጋሩም ሆነ ለሌሎች ህፃናት እና ሴቶች ደንታ የሌለው፣ ገና ሮጠውና ተጫውተው ያልጠገቡ ህፃናትን ለጥይት ማብረጃ እንዲሆኑ በሀሺሽ እያደነዘዘ ለጦር ግንባር የሚያሰልፍ ሰብአዊነት ፈፅሞ የማያውቅ እኩይና አረመኔ ቡድን በቃህ ሊለውና ሊታገለው ይገባል ነው ያለው፡፡

በትግራይ በአንዳንድ አካባቢዎች በአፋር ህዝብ ላይ ጦርነት የከፈተውን የህወሓት ጁንታ ተቃውመው የቆሙ የትግራይ ተወላጆች በእጅጉ ሊመሰገኑ እንደሚገባ መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፋር ህዝብና መንግስት ወደፊትም ለወንድም የትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ከሚመከለከታቸው የፌደራል መንግስትና የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በቅርበት የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.