Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መጠን በእጥፍ ጨምሯል

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2013 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የሳይበር ምህዳር ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መጠን በእጥፍ መጨመሩንየኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንት ኤጀንሲ ብሄራዊ የሳይበር ጥቃት የአደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዢን ሃላፊ አቶ ሰብለወይን ጸጋዬ እንደገለጹት÷ በ2013 በጀት አመት ከ2 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተሰንዝረዋል።

ይህም በ2012 ዓ.ም ከተሞከረዉ 1 ሺህ 80 አካባቢ ጥቃቶች ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን ያመላክታል ነው ያሉት።

በ2013 በጀት አመት ለተመዘገበው የሳይበር ጥቃቶች መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

ተቋማት አሰራራቸውን ቀደም ሲል ከነበረው ተለምዷዊ አጠቃቀም የኦንላይን አማራጮችን በስፋት መጠቀም መጀመራቸዉ ፣ከሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በሳይበር አማካኝነት ጫናዎች መፈጠራቸው እና በበርካታ ተቋማት ዘንድ ያለው ሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ክፍተት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ከእነዚህም የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ውስጥ 75 ነጥብ 25 በመቶ ምላሽ የተሰጠባቸው ÷ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ምላሽ እየተሰጣባቸው ያሉ መሆናቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የተደረጉት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢደርሱ ኖሮ በተቋማት እና በሀገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የስነ ልቦና ጫና ከፍተኛ እንደነበረም አቶ ሰብለወይን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ተቋማት መሰል የሳይበር ጥቃቶች ለመከላከል ጥቃቱን መከላከል የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ፣ የሰው ሃይላቸውን በዘርፉ የሰለጠነ እና ብቁ ማድረግ እንዲሁም ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.