Fana: At a Speed of Life!

አጣዬና አካባቢው እንዳይረጋጋ የሚሰሩ አካላትን ከህወሓትና ሸኔ እኩል መታገል ይገባል-ዶ/ር አህመዲን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አጣዬና አካባቢው እንዳይረጋጋ የሚሰሩ አካላትን ከህወሓትና ሸኔ የሽብር ቡድኖች እኩል መታገል እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አህመዲን መሐመድ ገለጹ፡፡

የአጣዬ ከተማ ወጣቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአካባቢው ኮማንድ ፖስት፣ ከፌደራልና ከክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አጣዬን መልሶ ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ በመሆኑ ወጣቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደጉም ዶ/ር አህመዲን መሐመድ ጠይቀዋል፡፡

ወጣቶቹ በፀጥታና ደህንነት፣ የመልሶ ግንባታ እና የመልካም አስተዳደር ጎዳዮች ዙሪያ ያላቸውን ጥያቄዎች አንስተው ውይይት አድርገዋል፡፡

የአጣዬና አካባቢው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ጀነራል ደስታ አብቼ÷ የህወሓት የሽብር ቡድን ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠር ሀገር ለመበተን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

አሁን ይህ ቡድን ግብዓተ መሬቱ እየተፈፀመ ነው ያሉት ጀነራሉ÷ ሞቱን ለማፋጠን ወጣቶች መከላከያን በመቀላቀል ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ፃዲቅ በበኩላቸው ÷የአጣዬ ከተማ ተመልሳ እንዳትገነባ የማይፈልጉ ሃይሎች አሁንም የተለያዩ አሉባልታዎችን ማሰራጨት ላይ መጠመዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ሃይሎችም በጋራ መመከት እንደሚገባ ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት፡፡

ወጣቶቹ የከተማዋ መልሶ ግንባታ እንዲፋጠንና በከተማዋ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸው የጠየቁ ሲሆን÷ ከተማዋ እንዳትረጋጋ በውስጥ እየሰሩ ያሉ አካላትን በጋራ እንደሚታገሉ ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውንም ከሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.